ብሔራዊ የትምህርት ትረስት ፈንድ ስትራቴጂ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር ብሔራዊ የትምህርት ትረስት ፈንድ ስትራቴጂን ይፋ አድርጓል።
ሚኒስቴሩ ብሔራዊ የትምህርት ትረስት ፈንድ ስትራቴጂውን ይፋ ያደረገው ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ከተውጣጡ ባለድርሻዎች ጋር የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ስድስት ወራት የዘርፍ ዕቅድ አፈጻጸምን በገመገመበት መድረክ ላይ ነው።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በወቅቱ እንዳሉት÷ ስትራቴጂው እንደ ሀገር እየተተገበረ ያለውን የ”ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄን በተደራጀ መንገድ ማስቀጠልን ታሳቢ ያደረገ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እየተተገበረ የሚገኘው ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በዘርፉ በርካታ ስራዎችን ለማከናወን ዕድል መፍጠሩን ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
ብሔራዊ የትምህርት ትረስት ፈንድ ስትራቴጂ ወደ ተግባር ሲገባ እየተመዘገበ ያለውን ውጤት በከፍተኛ ደረጃ ለማሻሻል እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
በተለይም የፋይናንስ አቅምን በወጉ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የትምህርት ዘርፉን ጥራት ለማረጋግጥ የተሰጠውን ትኩረት በመደገፍ ረገድ ድርሻው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል ዜጎች ፍትሃዊና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ሲሆን፤ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሻሻል በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸው ይታወቃል።
በይስማው አደራው