የመዲናዋ ሆቴሎች ለአፍሪካ እንግዶች የኢትዮጵያን እንግዳ ተቀባይነት የሚያንጸባርቅ መሥተንግዶ…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሆቴሎች አስፈላጊውን ዝግጅት በማጠናቀቅ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ተሳታፊ እንግዶችን መቀበል ጀምረዋል አለ የአዲስ አበባ ሆቴል ባለቤቶች ማህበር፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አስቴር ሰለሞን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የአዲስ አበባ ሆቴሎች የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ተሳታፊ እንግዶችን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገዋል።
አሁን ላይም ሆቴሎች ለአፍሪካውያን እንግዶች የኢትዮጵያን የእንግዳ ተቀባይነት ባሕል በተላበሰ መልኩ አቀባበል እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ሆቴሎች ለእንግዶቹ የሚሰጡት አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ፣ ደረጃውን የጠበቀና የኢትዮጵያን ባህል የሚያንጸባርቅ እንዲሆን በቁርጠኝነት መሰራቱን ነው የገለጹት፡፡
በተለይም ሆቴሎች አፍሪካውያን የጉባዔው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የቡና አፈላል ሥርዓት በሚገባ እንዲረዱ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም እንግዶች በቆይታቸው አይረሴ ጊዜን እንዲያሳልፉ ባሕላዊ ምግቦች፣ የኢትዮጵያን ብዝሃነት የሚያሳዩ ባሕላዊ አለባበስ እና ውዝዋዜዎች እንዲሁም ሌሎች ኩነቶች መሰናዳታቸውን አብራርተዋል፡፡
ሆቴሎች ለጉባዔ ተሳታፊ እንግዶች በተመጣጣኝ ዋጋ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት እንዲሰጡ ስምምነት ላይ መደረሱን ወ/ሮ አስቴር አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የውሃ፣ መብራት፣ ስልክ እና ሌሎች አገልግሎቶች መቆራረጥ እንዳያጋጥም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጥሩ እመርታ እያሳየ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ይበልጥ ለማጠናከር ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሕብረተሰቡ እንግዶችን በተለመደው የኢትዮጵያ እንግዳ አቀባበል ሥርዓት በማስተናገድ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡
ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በ48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ም/ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ።
በመላኩ ገድፍ