ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከሌሴቶና ሞሮኮ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከሌሴቶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌጆን ምፖትጆአኔ እና ከሞሮኮ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቡሪታ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ጌዲዮን (ዶ/ር) ከሌሴቶ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሌጆን ምፖትጆአኔ ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ውጤታማ በሆነችባቸው ዘርፎች ለሌሴቶ ልምዷን ለማካፈል ዝግጁ እንደሆነች መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፋና ዲጂታል ገልጿል፡፡
ሌጆን ምፖትጆአኔ በበኩላቸው ÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ በግብርና፣ ጤና እና ቱሪዝም ዘርፍ ልምድ ለመቅሰም ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል
ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የኮሪደር ልማት ሥራዎች አስደናቂ መሆናቸውን ነው ያወሱት፡፡
ሁለቱ ሚኒስትሮች በሁለትዮሽ እና አህጉራዊ የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውም ተጠቁሟል፡፡
በተመሳሳይ ጌዲዮን (ዶ/ር) ከሞሮኮ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቡሪታ ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን መድረኮች ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
በቀጣይ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በማካሄድ ግንኙነቱን ለማጠናከር መግባባት ላይ መድረሳቸው ተመላክቷል፡፡
ውይይቱ ከ48ኛው የአፍሪካ ህብረት መደበኛው የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ጎን ለጎን ነው የተካሄደው፡፡
👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ