ኢትዮጵያ ለጅቡቲ የምታቀርበው የንጹህ መጠጥ ውሃ ከ2063 አጀንዳ ትልም ጋር የሚጣጣም ነው – የአፍሪካ ሕብረት
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲጋላ-ጅቡቲ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ለጅቡቲ የምታቀርበው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ከ2063 አጀንዳ ትልም ጋር የሚጣጣም ነው አሉ የአፍሪካ ሕብረት የመሰረተ ልማትና ኢነርጂ ዘርፍ ኮሚሽነር ላታቦር ዲ ማታቦጅ ።
ኮሚሽነሯ ከ48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ጎን ለጎን ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም በአፍሪካ ዘላቂ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ንጽሕና የማረጋገጥ ጉዳይ አንዱ የኢኮኖሚ መሰረተ ልማት አካል ተደርጎ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።
በአህጉሪቱ ከ300 ሚሊየን በላይ ሰዎች የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አንደሌላቸው እና 780 ሚሊየን ሰዎች ደግሞ በቂ የንጽሕና መጠበቂያ እጦት ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ይህ መሰረታዊ ተግዳሮት በጤና፣ ኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ማነቆ ሆኖ መቀጠሉን እና አባል ሀገራት ችግሩን ለመቅረፍ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማረጋገጥ 30 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ ይህንን ኃብት ለማሰባሰብ ጥረቶች መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በራስ አቅም አቅዶ የመፈጸም ተግባር በምሳሌነት መውሰድ ይገባልም ነው ያሉት።
እንዲሁም በአዲጋላ-ጅቡቲ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ለጅቡቲ የምታቀርበው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ከ2063 አጀንዳ ትልም ጋር የሚጣጣም መሆኑን አውስተዋል፡፡
ተግባሩ በሌሎች ሀገራት ዘንድ በአርዓያነት የሚወሰድ እንደሆነ ተናግረዋል።
በመራኦል ከድር