Fana: At a Speed of Life!

80 በመቶ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓትን በሀገር ውስጥ ማሟላት ተቻለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 80 በመቶ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓት በሀገር ውስጥ አቅራቢዎች ማሟላት ተችሏል አለ።

የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎች ጥራታቸውን የጠበቁ የተለያዩ ግብዓቶች እንዲያቀርቡ ቅድሚያ ተሰጥቷል፡፡

ይህም መንግሥት የጀመረውን ሀገር በቀል ኢኮኖሚን ለማበረታታትና የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ያለመ ነው ብለዋል።

ከቀረቡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ግብዓቶች የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመር አንዱ ሲሆን፥ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 3 ሺህ 944 ትራንስፎርመሮች ከሀገር ውስጥ አምራቾች ቀርበው አገልግሎት ላይ ውለዋል ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ ከ32 ሺህ በላይ ኢንሱሌተሮች፣ ከ97 ሺህ በላይ የትራንስፎርመር ፕሮቴክሽን ዕቃዎችን፣ ከ32 ሺህ ሜትር በላይ ኮንዳክተርና ኬብሎችን እንዲሁም ከ201 ሺህ በላይ የተለያዩ የሀርድዌር ዕቃዎች በሀገር ውስጥ አቅርቦት ተሸፍኗል፡፡

አገልግሎቱ የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት ጥራት ያለው ግብዓት እንዲያቀርቡ አስፈላጊውን እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ ነው የገለጹት።

አምራቾችም ከአገልግሎቱ ጋር ውል በመዋዋል ደረጃቸውን የጠበቁ ግብዓቶችን እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

አገልግሎቱ ከደንበኞች ለሚቀርቡለት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥያቄ በፍጥነት እንዳይመልስ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ የግብዓት አቅርቦት ውስንነት ነው።

ችግሩን ለመፍታት ሀገር በቀል አምራቾች በማበረታትና የጎደለውን ከውጭ በሟሟላት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ አንዋር አመልክተዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.