Fana: At a Speed of Life!

የአንድነት፣ የታማኝነት፣ የሀገር ባለቤትነት ዕሴት የሆነው የዓድዋ ድል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓድዋ ድል የአንድነት፣ የታማኝነት፣ የሀገር ባለቤትነት እና ኃላፊነት ዕሴት ነው አሉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር)።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ምስረታ 2ኛ ዓመትን በማስመልከት “የዓድዋ ትሩፋት ለዛሬዋ ኢትዮጵያ እና ለነገው ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ የትውልድ ስብዕና ግንባታ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል መማር ይገባዋል በሚል ሀሳብ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው፤ የዓድዋ ድል የሚገባውን ትኩረት እና ቦታ እያገኘ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ለአብነትም በአዲስ አበባ ከተማ የተገነባውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ጠቅሰዋል።

ሁሉም ሚናውን በመለየት የድርሻውን በመወጣት ባበረከተው አስተዋጽዖ የተገኘው የዓድዋ ድል በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የጎላ ስፍራ እንዳለው አንስተዋል።

የፖለቲካ ቁርሾ እና ሌሎች ችግሮች ከሀገር በታች እንደሆኑ ከራስ መንገሻ መማር እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ረጅም የባሕር በር የነበራት ሀገር የባሕር በር ማጣት የለባትም ብለዋል።

ጥያቄው የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበው፤ ከዓድዋ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ዘርፎች ላይ አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ መማር ይገባል ብለዋል።

በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የዓድዋ ድል እንዲዘከር እና እንዲተዋወቅ መስራት እንደሚገባ ገልጸው፤ ድሉ ለአፍሪካውያን ከዋና ዋና የዓለማችን ክስተቶች መካከል የበለጠ ሚና እንዳለው ነው የተናገሩት።

ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዓድዋ ትሩፋት ትውልዱ በርካታ ትምህርት የሚወስድበት ነው ብለዋል።

ዛሬ ላይ ምን መደረግ እንዳለበት እና ወደፊት ምን መስራት እንደሚጠበቅ የምንመለከትበት ነው በማለት ገልጸው፤ ዓድዋ የጦርነት ድል ብቻ ሳይሆን የአንድነት፣ የታማኝነት፣ የሀገር ባለቤትነት እና ኃላፊነት ዕሴት ጭምር ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ድሉ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶችን በመተው ጠንካራ መሰረት ማስቀመጥ የቻሉበት በመሆኑ ትምህርት ልንወስድበት ይገባል ነው ያሉት።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.