Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በዓለም ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ ናት – ጄፍሪ ሳክስ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ ናት አሉ በተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት መፍትሄ ጥምረት ፕሬዚዳንት ጄፍሪ ሳክስ (ፕ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከጄፍሪ ሳክስ (ፕ/ር) ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጄፍሪ ሳክስ (ፕ/ር) ጋር መወያየት ሁልጊዜም አስደሳች መሆኑን ገልጸው፤ በቆይታቸውም በዘላቂ ልማት፣ በኢኮኖሚ እድገት እና ለአፍሪካ ልማት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል።

ውይይቱን ተከትሎም፣ ኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ጄፍሪ ሳክስ (ፕ/ር) ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እጅግ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልጸው÷ ይህንንም በተጨባጭ ለመረዳት በአዲስ አበባና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የታዩትን የኢኮኖሚ ለውጦች መመልከት በቂ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለያዩ ወቅት ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ወቅት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ የልማትና የዕድገት ለውጦችን መታዘባቸውን ጠቅሰዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ግንባታ፣ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች፣ የመንገድ መሠረተ ልማት መስፋፋት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የመሳብ አቅም መጨመርን በአብነት አንስተዋል።

ለዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ አስተዋፅኦ ማበረከቱን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያ የመጪውን ጊዜ አርቃ በማሰብና በማለም የምትተጋ ታላቅ ሀገር መሆኗን በተግባር አረጋግጣለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የፀሐይ፣ የንፋስና የጂኦተርማል ኃይል እምቅ አቅም እንዳላት በማንሳት÷ በተለይም በገጠራማ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን በአካል መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ይህም የአርሶ አደሩን ምርታማነት ከማሳደጉ ባለፈ የኑሮ ደረጃውን እያሻሻለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ በሜካናይዜሽንና በኤሌክትሪፊኬሽን ሲታገዝ ምርታማነቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምርም ጠቁመዋል።

በግብርናው ዘርፍ ኢትዮጵያ እያሳየች ያለው ውጤት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው÷ በተለይም በስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት ሀገሪቱ ራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎችም መትረፍ እንደምትችል ማሳያ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

አፍሪካ አሁን አንድነቷን ይበልጥ ማጠናከር ያለባት ወቅት ላይ ትገኛለች ያሉት ጄፍሪ ሳክስ (ፕ/ር)÷ አህጉራዊ የንግድ ልውውጥንና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ሀገራት በመንገድ፣ በባቡር እና በኃይል ማመንጫ የልማት ስራዎች ተሳስረው መስራት እንዳለባቸው መክረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.