በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ እየተፈተነ የሚገኘው ሪያል ማድሪድ…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር በአዲስ አቀራረብ በሊግ ቅርፅ መደረግ ከጀመረ ወዲህ በመድረኩ እየተፈተነ ይገኛል፡፡
በ2024/25 የውድድር ዘመን ውድድሩ በአዲስ አቀራረብ መደረግ በጀመረበት ወቅት ሪያል ማድሪድ 16ቱን ለመቀላቀል የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
በወቅቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አደርጎ 16ቱን የተቀላቀለው ሪያል ማድሪድ በመድረኩ መጓዝ የቻለው እስከ ሩብ ፍጻሜ ብቻ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በዚህኛው የውድድር ዓመትም ሪያል ማድሪድ 16ቱን ለመቀላቀል የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ለማድረግ ተገድዷል፡፡
በ2025/26 የውድድር ዓመት በሊግ ቅርጽ ካደረጋቸው 8 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አምስቱን ሲሆን በሦስቱ ደግሞ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡
በዚህም 15 ነጥብ በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 9ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ተከትሎ 16ቱን ለመቀላቀል የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ሪያል ማድሪድ በመድረኩ 16ቱን ለመቀላቀል በሚያደርገው ጉዞ የጥሎ ማለፍ ጨዋታውን ከቤኔፊካ ጋር ያደርጋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች በዚህ የውድድር ዓመት በመድረኩ በስምንተኛ ሳምንት መርሐ ግብር የተናገኙ ሲሆን ቤኔፊካ 4 ለ 2 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡
በፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ የሚመራው ቤኔፊካ ሳይጠበቅ ሪያል ማድሪድን ማሸነፉ በወቅቱ መነጋገሪያ ነበር፡፡
የ15 ጊዜ የመድረኩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ጨምሮ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አቀራረብ እየተደረገ በሚገኘው ውድድር እየተፈተነ ይገኛል፡፡
የጥሎ ማለፍ ድልድል ዕጣ ሲወጣ ሁለቱ ቡድኖች በድጋሚ ተገናኝተዋል፡፡
አወዛጋቢው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ በድጋሚ የቀድሞ ቡድናቸውን በተቃራኒው የሚገጥሙ ይሆናል፡፡
ጆዜ በሪያል ማድሪድ የአሰልጣገኝነት ዘመን ቆይታቸው በርካታ ስኬታማ ዓመታትን ማሳለፋቸው ይታወሳል፡፡
ጆዜ ሞሪኒሆ ከዛሬው ጨዋታ አስቀድመው በሰጡት አስተያየት የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ንጉስ በሆነው ሪያል ማድሪድ ላይ ያደረግነውን እናውቃለን ብለዋል፡፡
በቅርቡ ባደረግነው ጨዋታ ቆስለዋል፣ የቆሰለ ንጉሥ ደግሞ አደገኛ ነው ስለዚህ ተጫዋቾቼ ለሪያል ማድሪድ ቀላል ግምት እንዳይሰጡ አስጠንቅቂያለሁ ነው ያሉት።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው በሁሉም ውድድር 10 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሪያል ማድሪድ አራቱን ሲያሸንፍ ቤኔፊካ በአምስቱ ድል አድርጎ በአንዱ አቻ ተለያይተዋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት ላይ በስታዲዮ ዳ ሉዝ የጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
የሁለቱ ቡድኖች የመልስ ጨዋታ በቀጣይ ሳምንት በቤርናባው የሚደረግ ሲሆን የድምር ውጤት አሸናፊው ቡድን 16ቱን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ