Fana: At a Speed of Life!

ሰላም የኦሮሞ ህዝብ ዋነኛ እሴቱ እና መለያው ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰላም የኦሮሞ ህዝብ ዋነኛ እሴቱ እና መለያው ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቄለም ወለጋ ዞን የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትን በጎበኙበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኦሮሞ ህዝብ ሰላም ወዳድ መሆኑን ለማሳየት ልጆቹን ነጋሳ እና ነጋሶ በማለት ይሰይማል ብለዋል።
ህዝቡ ሰላም ዋነኛ እሴቱ እና መለያው እንደሆነ ገልጸው፤ ልዩነትን በውይይት እንደሚፈታ ለማሳየት ልጆቹን አራርሳ (አስታራቂ) ብሎ የሚሰይም ድንቅ ጥበብ የተጎናጸፈ ህዝብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በየትኛውም ችግር ሊከሰት የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፤ ችግሩን በንግግር እና በውይይት መፍታት ጥበብ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የወለጋ አካባቢ ባለፉት ጊዜያት የሰላም እጦት ገጥሞት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተጀመረውን ልማት እና ብልጽግና ለማስቀጠል ሰላምን ማጽናት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ልዩነቶች ቢያጋጥሙ እንኳን በምክክር መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በትጥቅ ትግል ጫካ የነበሩ ወንድሞች ፍላጎታቸውን በውይይት ለማሳካት ማህበረሰቡን መቀላቀላቸው በመቻላቸው አድናቆታቸውን ገልጸው፤ የቀሩ ወንድሞችም በሰላማዊ መንገድ ህብረተሰቡን ተቀላቅለው የተጀመረውን ልማት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አካባቢው ያለውን የቡና እና እንስሳት ልማት እምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ሰላምን ማጽናት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
አሁን በአከባቢው የታየው የልማት ጭላንጭል ወደ ተሟላ ብርሃን እንዲሸጋገር ሁሉም ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል ብለዋል።
ልዩነቶችን እና የፖለቲካ ፍላጎቶችን በውይይትና በንግግር ብቻ መፍታት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ህዝቡ ጫካ ያሉ ልጆቹን በመምከር እና በመገሰጽ የሰላም አማራጭን እንዲከተሉ ግፊት በማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የኃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች እና ምሁራን ሰላምን በማጽናት ሂደት የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው ነው ያሉት።
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.