2 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት ተችሏል – ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እስከ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን የሚደርስ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ በማምረት መተካት ተችሏል አሉ የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)።
የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመርቋል።
ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በከርሰ ምድሯና ገጸምድሯ የያዘቻቸውን በዓይነትና በብዛት የበረከቱ ማዕድናትን አውጥተን እሴትን ጨምረን ከድህነት የምንወጣው መቼ ነው የሚለውን ቁዘማ ከለውጥ መንግሥት በኋላ የማዕድን ዘርፍን የኢኮኖሚ ዋና ምሰሶ በማድረግ የዘርፉን ፍሬዎች ማጣጣም ጀምራለች።
የማዕድን ዘርፍ በወጪ ንግድ ዘርፍ ላይ ያሳየው ከፍተኛ ዕድገት እንዲሁም በሀገር ደረጃ ስትራቴጂክ የገቢ ምርቶችን በመተካት ላይ እየተመዘገበ ያለው ዕድገትና ለኢኮኖሚ ያለው ገንቢ አበርክቶ ዓይነተኛ ማሳያ ሆኖ ይገለጻል ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት እና የተመረቀው የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ እያደገ ለመጣው የማዕድን ዘርፍ ዕድገት ቀጣይነት ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ ማዕድናት ሊለማ የሚችል የድንጋይ ከሰል በተለምዶ ጥቁር ወርቅ የምንለው ሀብት ካላቸው ሀገራት ተርታ እንደምትመደብም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ሀብቱ ቢኖራትም እስከ ባለፉት ሁለት ዓመታት እስከ 300 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በማውጣት የታጠበ ድንጋይ ከሰል ከውጪ እንደምታስገባ አስታውሰዋል።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ለሲሚንቶ፣ ብረት፣ ሴራሚክና ሌሎች ለፋብሪካዎች ፍጆታ የሚውል እስከ 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን የሚደርስ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማምረት መተካት ተችሏል ብለዋል።
ይህም መንግሥት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ሀብቱ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ለሀገር በቀል ኩባንያዎች የከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ በመደረጉ እንደሆነ አመልክተዋል።
በተለይም የድንጋይ ከሰል ምርት በተገቢው ሁኔታ በመቅረቡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የምርት መጓደል እንዳይኖር በመደረጉ የሲሚንቶ ገበያ እንዲረጋጋና ለኮንስትራክሽን እንዱስትሪው በአስተማማኝ እንዲቀርብ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
ሚዲሮክ ኢንቨስትመንት ባጠረ ጊዜ እስከ 200 ቶን በሰዓት የሚያመርት በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ የተሟላ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ መገንባቱ የድንጋይ ከሰል አቅርቦቱን ዘላቂነት ያለው እንዲሆን ይረዳናል ብለዋል።
ለፋብሪካው መሳካት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ አስተዋጽዖ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
እንደ ድጋይ ከሰል ሁሉ የሀገሪቱን የሴራሚክስ ፍላጎት በሀገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለመተካት ግዙፍ ኩባንያዎች ግንባታ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ እስከ 3 ወራት ባለው ጊዜ ተጠናቅቀው ማምረት እንደሚጀምሩ ተናግረዋል።
ይህም ለቤት ግንባታው ዘርፍ አስቻይ ዋጋና ዘላቂነት ያለውን አቅርቦት በመፍጠር በቀጣይ የታሰበውን የመኖሪያ ቤት ግንባታ በአጠቃላይ የሕንፃ ግንባታ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
በአድማሱ አራጋው