Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት ለግሉ ዘርፍ በሰጠው ማበረታቻ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጀማል አህመድ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ በሰጠው ማበረታቻ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል አሉ።

የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የሚያበረታታ ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ተግባር ገብቷል።

በዚህም መንግሥት ለግሉ ዘርፉ በሰጠው ጥኩረት እና ማበረታቻ የሀገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ እና ተኪ ምርትን በማስፋት አላስፈላጊ የውጭ ምንዛሪ ጫናን መቀነስ መቻሉን አንስተዋል።

የድንጋይ ከሰል ምርት ቀደም ሲል ከውጭ ሀገራት ይገባ እንደነበር አስታውሰው÷ የአርጆ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ ለማምረት ያስችላል ብለዋል።

ፋብሪካው ከውጭ የሚመጣ ጥሬ እቃ እና ኬሚካል እንደማይጠቀም ገልጸው፤ በሀገር ውስጥ ያለ የተፈጥሮ ሀብት ብቻ በመጠቀም የድንጋይ ከሰል አጥቦ እና አቀነባብሮ ምርት የሚያቀርብ መሆኑን አብራርተዋል።

በሰዓት 200 ቶን የድንጋይ ከሰል የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካው÷ ለወረቀት እና ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርቱን ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት ፈርሟል ብለዋል።

ፋብሪካው ጥራት ያለው ምርት በማቅረብ በኢትዮጵያ ያሉ ፋብሪካዎች ስራቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲያከናውኑ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በአካባቢው ያከናወነው የመጀመሪያ ግንባታ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ሌሎች ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ ማቀዱን ጠቁመዋል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.