Fana: At a Speed of Life!

በሲዳማ ክልል ከበጋ መስኖ ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል ከበጋ መስኖ ልማት እስካሁን 10 ሚሊየን 460 ሺህ ኩንታል ምርት ተሰብስቧል አለ የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ።

በቢሮው የአትክልት እና መስኖ ልማት ዳይሬክተር አምሳሉ አርጋው ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በክልሉ ያለውን የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውሃን በመለየትና አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ ሥነ ምሕዳሩን ታሳቢ ያደረገ የበጋ መስኖ ልማት ስራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ94 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሁለት ዙር በመስኖ በማልማት ወደ 21 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙርም 80 ሺህ 890 ሄክታር መሬት በማልማት 18 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸው÷ ከ40 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በኩታ ገጠም እርሻ መልማቱን ጠቁመዋል።

በክልሉ ከ275 ሺህ በላይ ዜጎች በመስኖ ልማት ውስጥ መሳተፉንና እስካሁን 10 ሚሊየን 460 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች ያመረቷቸውን ምርቶች በቀጥታ ለሸማቹ ማሕበረሰብ ማቅረብ እንዲችል ገበያ ትስስር የመፍጠር ስራ መከናወኑንም አብራርተዋል።

በመስኖ ልማት ስራ ለብዙ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ያሉት አቶ አምሳሉ÷ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች እንዳይፈጠሩ እንዲሁም ከአመለካከትና ክህሎት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዳይኖሩ በየደረጃው ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች መከናወኑን አመልክተዋል።

በሁለተኛው ዙር የመስኖ እርሻ ከ13 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት 2 ነጥብ 9 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ተናግረዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.