ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌስትሪም” የተሰኘ የዲጂታል አሰራር አስጀመረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም “ቴሌስትሪም” የተሰኘ የዲጂታል አሰራር በይፋ አስጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራአስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንዳሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮም የሚሰጠውን አገልግሎት የላቀ ለማድረግ የሚያስችል ተግባር እያከናወነ ነው።
“ቴሌስትሪም” የተሰኘው የዲጂታል አሰራር ለደንበኞች ከሚሰጠው ከፍተኛ ጥቅም ባለፈ የኢትዮጵያን ገቢ ለማሳደግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
ለአዳዲስ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለይዘት ፈጣሪዎች እንዲሁም የዜጎችን የዲጂታል ተጠቃሚነት ለማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
ዜጎች የትምህርት እና የጤና መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙና ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚረዳ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ቴሌስትሪም ለሁሉም አገልግሎት የሚሰጥ የዲጂታል አሰራር መሆኑን ጠቅሰው፤ የሀገር ውስጥ ቻናሎችን ተደራሽነት የሚያሰፋ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በተለይም የሚዲያ ስነ ምህዳሩን በእጅጉ የሚያዘምን አገልግሎት እንደሆነ የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ የመደበኛ ብሮድባንድ አገልግሎት አሰጣጥን የሚያቀላጥፍ የዲጂታል አሰራር መሆኑን አብራርተዋል።
በየሻምበል ምህረት