Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ 5ኛውን ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ኢትዮጵያ ታምርት፣ አዲስ አበባ ትበልፅግ” በሚል መሪ ሀሳብ ለ5ኛ ጊዜ የሚካሄደውን ከተማ አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዛሬው ዕለት አስጀምረዋል።

ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ባለፉት ዓመታት ተዘግተው የነበሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ምርታማነት በመመለስ፣ ፋይናንስና የማምረቻ ቦታዎችን በማመቻቸት፣ የገበያ ትስስርና የእውቀት ሽግግር በመፍጠር ረገድ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

በዚህም የከተማ አስተዳደሩ በወሰዳቸው ርምጃዎችና በዘርፉ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ ችለናል ነው ያሉት።

በተለይም በተኪ ምርቶች ረገድ የሀገር ውስጥ ምርት ተጠቃሚነት ባህል እያደገ መጥቷል ያሉት ከንቲባዋ፥ አምራቾች በቀጣይም በየዕለቱ የምርት ጥራትን በማላቅ ተወዳዳሪነታቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የንቅናቄ መርሐ ግብሩ አካል የሆነ ኤክስፖ በኮንቬንሽን ሴንተር የተከፈተ ሲሆን፥ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ኤክስፖ ላይ የጨርቃጨርቅ፣ የሕክምና፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች በስፋት ቀርበዋል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎችም በአምራች ኢንዱስትሪዎች ተመርተው የቀረቡ ምርቶችን እንዲጎበኙና እንዲሸምቱ ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.