ሦስት የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን ያጣጣመው ፈርጣማ ኮከብ – ፔፔ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አልሸነፍ ባይነትና ደመ ሞቃትነቱ ኃይል ከተቀላቀለ አጨዋወቱ ጋር ተዳምረው የእግር ኳስ ቴክኒካዊ አቅሙን የሸፈኑበት ኮከብ ነው፤ ፖርቹጋላዊው የሪያል ማድሪድ የቀድሞ ተከላካይ ፔፔ፡፡
በተለይም በተወዳጁ የኤልክላሲኮ ደርቢ የጨዋታው ግለት እንዲያይል ከሚያደርጉ እልኸኛ ተጫዋቾች መካከል ፔፔ ተጠቃሽ ነው፡፡
ፔፔ በሚል ስሙ የሚታወቀው ፖርቹጋላዊ ኮከብ ኬፕለር ላቭራን ሊማ ፌሬራ የተወለደው በብራዚል አላጎስ ግዛት ማሲዮ ከተማ ሲሆን፥ እግር ኳስንም የጀመረው በትውልድ ከተማው በሚገኘው ኮሪንቲያንስ አላጋኖ ነበር፡፡
በ18 ዓመቱ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ፖርቹጋል አቀና ፤ በዚያም በማርቲሞ የወጣቶች ቡድን አልፎ በፈረንጆቹ 2001 እግር ኳስን በፕሮፌሽናል ደረጃ መጫወት ጀምሯል፡፡
በማርቲሞ ቆይታው ተሰጥኦውን ማሳየት የቻለው ፔፔ በ2004 ፖርቶን በመቀላቀል ሁለት ጊዜ የፖርቹጋል ፕሪሚየራ ሊጋ ሻምፒዮን በመሆን ስኬታማ ጊዜያትን አሳልፏል፡፡
በ2007 ከፖርቶ ወደ ሪያል ማድሪድ በማቅናት ከሰርጂዮ ራሞስ ጋር በፈጠሩት ጠንካራ ጥምረት የሎስ ብላንኮዎቹ ሁነኛ የኋላ ደጀን በመሆን ለ10 ዓመታት በሳንቲያጎ በርናባው ደምቋል።
በተለይም ተንሸራትቶ ኳስ በማስጣል ብቃት፣ በፍጥነቱ እንዲሁም የመከላከል ቀጣናውን በሚገባ በመሸፈን ቴክኒካዊ አረዳዱ ድንቅ ተጫዋች መሆኑ የሚነገርለት ፔፔ ከምንጊዜም ምርጥ ተከላካዮች ውስጥ አንዱ ነው።
ከእግር ኳስ ክህሎቱ ባለፈ በመሪነት ሚናው እና በትልቅ ጨዋታ የአሸናፊነት ሥነልቦናው የሚደነቀው ተጫዋቹ ፥ በ10 ዓመታት የማድሪድ ቆይታው 334 ጨዋታዎችን አድርጓል።
በእነዚህ ዓመታት በተለይም ሪያል ማድሪድ በአውሮፓ መድረክ በነገሰባቸው 2014፣ 2016 እና 2017 ሦስት ጊዜ የሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን አሳክቷል።
በተጨማሪም ሦስት የላሊጋ ዋንጫዎችን ጨምሮ በሀገር ውስጥና አህጉራዊ ውድድሮች በስኬት የታጀቡ ዓመታትን ባሳለፈበት በርናባው በ2014 የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመባል ተመርጧል።
በ2017 ከሪያል ማድሪድ ጋር ከተለያየ በኋላ ለቱርኩ ክለብ ቤሺክታሽ የተጫወተ ሲሆን ፥ በ2019 ወደ ሀገሩ ተመልሶ የቀድሞ ክለቡን ፖርቶ ተቀላቅሏል።
ከ12 ዓመታት በኋላ ፖርቶን ዳግመኛ በመቀላቀል ተጨማሪ ሁለት የፕሪሚየራ ሊጋ ዋንጫዎችን ጨምሮ ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ ችሏል።
ፔፔ ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ብዙ ጨዋታዎችን በማድረግ (141) ከቅርብ ወዳጁ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና ዦአዎ ሞቲንሆ በመቀጠል ሦስተኛው ተጫዋች ነው።
በሜዳ ውስጥ በሚፈጠሩ እሰጣገባዎች ውስጥ የማይታጣው ፔፔ ሃይል ባመዘነበት አጨዋወቱና እልህ በተሞላባቸው እንቅስቃሴዎቹ ለተደጋጋሚ ቀይ ካርዶች ተዳርጓል።
በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ሕይወቱ 17 ቀይ ካርዶችን የተመለከተ ሲሆን፥ 212 ጊዜ ቢጫ ካርዶች በዳኞች ተመዝዘውበታል።
በሜዳ ውስጥ ነውጠኛ መሆኑ ስሙን የሸፈነበት ፔፔ ለ23 ዓመታት ከ74ዐ በላይ ጨዋታዎችን አድርጓል፤ ራሱን እየጠበቀ በወጥ ብቃት ለረጅም ዓመታት በመዝለቁ ለብዙዎች ምሳሌ ተደርጎ ይነሳል።
ከሀገሩ ልጅ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያለው ፔፔ ፥ ከፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር ያሳኩትን የዩሮ 2016 ዋንጫ ጨምሮ በሪያል ማድሪድ በዋንጫ የታጀቡ ዓመታትን በጋራ አሳልፈዋል።
በዚህ ሳምንት 43ኛ ዓመቱን የሚደፍነው ፖርቹጋላዊው የቀድሞ ኮከብ ተከላካይ በ41 ዓመቱ ራሱን ከተጫዋችነት ማግለሉ አይዘነጋም።
በኃይለማርያም ተገኝ