በ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ 21 አዳዲስ የገጠር ከተሞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ…
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር ክልል ከ2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ 21 አዳዲስ የገጠር ከተሞችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት እየተጠናቀቀ ነው አለ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፡፡
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር እንዳሉት÷ ፕሮጀክቱ በአፍዴራና ዳሎል አካባቢ የሚገኙ የጨውና ፖታሽ አምራች ኢንዱስትሪዎችን እንዲሁም 21 አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ግንባታ የአፍሪካ ልማት ባንክ 16 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን÷ ቀሪው 84 ነጥብ 62 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚሸፈን አመልክተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ 375 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ የኤሌክትሪክ መስመር፣ 93 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እና የ85 ትራንስፎርመሮችን ተከላ ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
እስካሁን በተከናወነው ሥራ 278 ነጥብ 34 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመርና 33 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የ29 ትራንስፎርመሮች ተከላ መጠናቀቁን አቶ አንዋር ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
በዚህም 8 መንደሮችንና አንድ ፋብሪካን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን÷ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 14 ሺህ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 84 ነጥብ 46 በመቶ መድረሱን የተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው÷ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአካባቢው በማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ የግል ድርጅቶችን በማበረታታትና የማሕበረሰቡን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማነቃቃት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተመላክቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ