Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያስመዘገበችው ውጤት አፍሪካን በአጭር ጊዜ ውስጥ የምግብ ዋስትናዋን ከማረጋገጥ አልፋ ለዓለም ገበያ በቂ ምርት የማቅረብ አቅም እንዳላት የሚያሳይ ነው አሉ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የግብርና ባለሙያዎች፡፡

ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ የግብርናው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ በክላስተር የለማ የስንዴ ማሳን ተመልክተዋል።

በዓለም አቀፉ የዝናብ አጠር አካባቢዎች ምርምር ማዕከል የአፍሪካ አህጉር አስተባባሪ ዘውዴ ቢሻው (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተገበረችው ማሻሻያ በአህጉሪቱ በአርዓያነት የሚነሳ ውጤት አስመዝግባለች፡፡

ስንዴን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡንም አስተባባሪው ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡

ምቹ የፖሊሲ ማሻሻያ እና ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎች መሟላትለተመዘገበው ስኬት ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፉን በማሻሻል በአሁኑ ወቅት በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ ምርት እያመረተች እንደምትገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ናይጄሪያዊው ኬኒዲ ካጎ እና ዚምባቡዌያዊቷ ሲሲሊያ ሳንያሙየራ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መንግሥት ግብርናን ለማዘመን የተገበረው የሪፎርም ሥራ በዘርፉ ለአህጉሪቱ አርአያ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የተገበረው ሪፎርም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ቀዳሚ እንድትሆን አስችሏታል ነው ያሉት።

አፍሪካውያንም የኢትዮጵያን ፈለግ ተከትለው ከምግብ ተረጂነት መላቀቅ የሚያስችላቸውን ፖሊሲ ቀርጸው መስራት እንዳለባቸው የጉብኝቱ ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡

በመሳፍንት ብርሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.