በክልሉ ከ55 ሺህ በላይ ደንበኞች የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አግኝተዋል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ55ሺህ በላይ ደንበኞች አገልግሎት አግኝተዋል አለ የክልሉ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ፡፡
በደብረብርሃን ከተማ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችል የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ እመቤት ምትኩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን እየፈታ ነው፡፡
የተገልጋይን እንግልትና የጊዜ ብክነት ያስቀረ ነው ያሉት ምክትል ኃላፊዋ÷ አገልግሎት በጀመረባቸው ከተሞች በተደረገው ጥናት 96 በመቶ ደንበኞች ደስተኛ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
በ2ኛው ዙር በደብረ ብርሃን፣ ደብረ ታቦር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ከምቦልቻና ወልድያ ከተሞች ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡
እስካሁን 40 ተቋማት ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መግባታቸውን ጠቅሰው፥ በ3ኛ ዙር በ25 ከተሞች አገልግሎት ለመጀመር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳድር ከንቲባ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው÷ የልማት ግቦችን ለማሳካትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ማዕከሉ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
ደብረብርሃን ከተማ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት ያለበት መሆኑን ገልጸው፥ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ማዕከሉን በከተማዋ ለመጀመር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአላዩ ገረመው