Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ባንክ በተለያዩ መተግበሪያዎች የሚደረጉ የአቻ የዲጂታል ግብይቶችን በጊዜያዊነት አገደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክሪፕቶ ከረንሲን ጨምሮ ፈቃድ በሌላቸው የተለያዩ መተግበሪያዎች የሚደረጉ የአቻ የዲጂታል ግብይቶችን በጊዜያዊነት አግዷል፡፡

ባንኩ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው÷ በተዘረጉ የቁጥጥር ማዕቀፎች መሰረት በተደረገ ክትትል ግለሰቦች ከባንኩ ፈቃድ በሌላቸው የተለያዩ መተግበሪያዎች ግብይቶችን እየፈፀሙ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ግብይት ፍላጎት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገልጾ፤ ግለሰቦች ግብይት በሚፈፅሙበት ወቅት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በተለይም የዲጂታል ግብይቶች የገበያ ተለዋዋጭነትን፣ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ማሳሳትን፣ የሳይበር ወንጀልን፣ የግብይት ግልፀኝነት ችግሮችን የሚያስከትሉ እንዲሁም የህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የፋይናንስ ሽብርተኝነት ክልከላ ማዕቀፍ የሌላቸው መሆኑን አብራርቷል፡፡

ባንኩ ዲጂታል የግብይት ቴክኖሎጂዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል አጠቃላይ የቁጥጥር ማዕቀፍ በመዘርጋት እየሰራ መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

በቀጣይም የፋይናንስ መረጋጋትን እና የብሔራዊ የክፍያ ስርዓቱን ታማኝነት ለመጠበቅ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቆጣጣሪዎች እና ከሀገር ውስጥ ባለድርሻ አካላት ጋር ቀጣይነት ያለው ምክክር እንደሚደረግ ጠቁሟል፡፡

የግብይት ቁጥጥር ማዕቀፍ ይፋ እስከሚሆን ድረስ ክሪፕቶ ከረንሲን ጨምሮ ፈቃድ በሌላቸው የተለያዩ መተግበሪያዎች የሚደረጉ የአቻ የዲጂታል ግብይቶች የተከለከሉ መሆኑን ባንኩ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.