Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻል ይገባል – አቶ ጥላሁን ከበደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ያጋጠመንን የትምህርት ስብራት ለመጠገን የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል በዕውቀትና ክህሎት የታነጸ ትውልድ ማፍራት ይገባል አሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ።

በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን ኦሞራቴ ከተማ በሰዎች ለሰዎች ግብረሰናይ ድርጅት እና በትምህርት ሚኒስቴር የተገነባው የዳሰነች ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቋል።

አቶ ጥላሁን ከበደ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን ጠብቀው እየተገነቡ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር የትምህርት ዘርፍ የገጠመውን ስብራት ለመጠገን እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ዘመኑን የዋጀ ትምህርት ተደራሽ እንዲሆን መንግሥት ባከናወነው ተግባር ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው ብለዋል።

የትምህርት ዘርፍ የሁሉንም አካላት ድጋፍና ትብብር የሚፈልግ በመሆኑ ለውጤታማነቱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ ትውልዱ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኝ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተመረቁት ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ካለው የትምህርት መሰረተ ልማት ፍላጎት አንፃር በቂ ባይሆኑም በቀጣይ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶች እንደሚገነቡ አረጋግጠዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የትምህርት እድል እንዲያገኙ ለማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ34 ሺህ በላይ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን መገንባታቸውን አስታውሰዋል።

ትምህርት የእድገት መሰረት በመሆኑ ለትውልዱ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ ማደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

በክልሉ ኮሬ ዞን ኬሌ ከተማ የተገነባው የአማሮ ሞዴል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በትናንትናው ዕለት መመረቁ ይታወሳል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.