በአምራች ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው – አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአምራች ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው አሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል አባላት በሸገር ከተማ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡
አቶ መላኩ አለበል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የአምራች ዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማጠናከር የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ሁለንተናዊ አቅም ከማጎልበት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
የአምራቾችን ችግር ለመፍታት የተቋቋመው የአምራች ኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስልም ከተቋማቱ ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚኝ አመልክተዋል፡፡
ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የፋይናንስ እና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ለማሳለጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
በአምራቾች ዘንድ የሚስተዋሉ ችግሮችን የሚመለከታቸው ተቋማት የየራሳቸውን ኃላፊነት ወስደው መፍትሄ እንደሚሰጡም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራሮች በበኩላቸው÷ አምራቾች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኤፍሬም ምትኩ