Fana: At a Speed of Life!

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል – አፈ ጉባዔ ታገሰ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል አሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፡፡

“የዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ በዳኝነትና ዴሞክራሲ ተቋማት ቅንጅት ላይ የሚያተኩር ሀገራዊ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

አቶ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ የተከናወኑ መሠረታዊ የለውጥ ርምጃዎች የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሥርዓት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን በማሻሻል ቦርዱ ያለምንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት እንዲሠራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

መንግሥት ተቋሙ በሰው ኃይልና በሎጂስቲክስ እንዲደራጅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰው÷ ምርጫው ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲከናወን ምቹ መደላድል መፍጠሩን አመልክተዋል።

በቦርዱ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች ገለልተኝነትን በማረጋገጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ዴሞክራሲያዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሆኖ እንዲካሄድ በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በበኩላቸው÷ ቦርዱ ወደ ዲጂታል አሠራር እያደረገ ያለው ሽግግር የምርጫውን ተዓማኒነት ለማሳደግ ያለመ ነው ብለዋል።

የምርጫው ሒደት ነጻ፣ ፍትሐዊና አካታች እንዲሆን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.