Fana: At a Speed of Life!

የምገባ መርሐ ግብር ለትምሕርት ጥራት …

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ በክልሉ እየተተገበረ ያለው የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር ለትምሕርት ጥራት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው አለ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ እና የመማር ማስተማር፣ ምዘና ክፍል ኃላፊ ማቲዮስ ማልደዮ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ መርሐ ግብሩ የትምህርት ጥራትን ከሚያሳድጉ ጉዳዮች መካከል አንዱ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል።

መርሐ ግብሩ የማሕበረሰብ ንቅናቄ በመፍጠር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ በ2018 የትምህርት ዘመን ምገባው ተጠናክሮ እና ተስፋፍቶ እንዲቀጥል ተደርጓል ብለዋል።

ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በመምከር እና የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት በማሕበረሰብ አቀፍ ተሳትፎ በሁሉም ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች መርሐ ግብሩ እየተተገበረ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህም በ375 የቅድመ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በ180 1ኛ ደረጃ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ በ555 ትምሕርት ቤቶች ላይ የምገባ መርሐ ግብር እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ከ135 ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ መርሐ ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ማሕበረሰቡ 73 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

የአደጋ ስጋት ተጋላጭ ተብለው በተለዩ አካባቢዎች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች 56 ሺህ ተማሪዎችን የምገባ ተጠቃሚ ለማድረግ የ22 ሚሊየን ብር በጀት በመንግሥት መመደቡን ጠቁመዋል።

የምገባ መርሐ ግብር በተማሪዎች ላይ አዎንታዊ ለውጥ እያመጣ እንደሆነ የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ መርሐ ግብሩ ተግባራዊ በሆነባቸው አካባቢዎች የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ እና ከትምህርት ቤት የመቅረት ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ተረጋግተው መከታተል በመቻላቸው ውጤታቸው እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል።

የምገባ መርሐ ግብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት አቶ ማቴዎስ፤ በቀጣይ ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን ወደ መርሐ ግብሩ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዮናስ ጌትነት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.