የኢራን አዲሱ መንፈሳዊ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ …
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካና እስራኤል ከቀናት በፊት በኢራን ላይ በፈጸሙት የሚሳኤል ጥቃት በተገደሉት የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ቦታ ሁለተኛ ልጃቸው ሞጅታባ ኻሜኒ ተተክተዋል።
የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ኻሜኒ በኢራን ምንም አይነት የመንግሥት ቢሮ አገልግሎት ያልሰጡ፣ የአደባባይ ንግግሮችን በማድረግ የማይታወቁ ቢሆንም በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ከመጋረጃ ጀርባ ያላቸው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በዚህም የተነሳ የኢራን አዲሱ መሪ አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ ስማቸው በስፋት የሚነሳ ሰው ነበሩ።
በፈረንጆቹ 1969 በሰሜን ምስራቅ ማሻሃድ ከተማ የተወለዱት ሞጅታባ ኻሜኒ፤ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቴህራን አላቪ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
እንደ ኢራን መገናኛ ብዙሃን ዘገባ፤ ሞጅታባ ኻሜኒ በ17 ዓመታቸው የመከላከያ ሠራዊትን ተቀላቅለው ለስምንት ዓመታት በተካሄደው የኢራን-ኢራቅ ጦርነት ተሳትፈው ሀገራቸውን አገልግለዋል።
በፈረንጆቹ 1999 ሞጅታባ በኢራን ቅዱስ ከተማ ወደምትባለው ቆም በማቅናት የሺዓ መንፈሳዊ ትምህርትን ተከታትለዋል፡፡
ኢራን ለ36 ዓመታት የመሯትን አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ባጣችበት እና ችግር ውስጥ በገባችበት በአሁኑ ወቅት ሞጅታባ ኻሜኒ በአባታቸው ቦታ ተተክተው የኢራን መንፈሳዊ መሪ ለመሆን በቅተዋል።
አንዳንዶች አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸውን ፖሊሲዎች እንደሚያስቀጥሉ የገመቱ ሲሆን፤ አንዳንዶች ደግሞ የአሜሪካ እና እስራኤል የተቀናጀ ጥቃት አዲሱን አያቶላ ጫና ውስጥ እንደሚያስገባ አንስተዋል።
አባታቸውን፣ እናታቸውን፣ ባለቤታቸውን እና ልጃቸውን በአሜሪካ-እስራኤል የአየር ጥቃት የተነጠቁት አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ፤ ቀጣይ የሁለቱ ሀገራት ኢላማ ስለመሆናቸው እየተነገረ ነው፡፡
ሹመቱ ለአዲሱ መሪ አጣብቂኝ እንደሆነ ብዙዎች እየገለጹ ቢሆንም፤ በርካታ ኢራናውያን ሀገራቸው አሁን ካለችበት ቀውስ ሊያላቅቋት የሚችሉት አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ እንደሆኑ በማንሳት ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
አንዳንዶች ደግሞ የኢራን መንፈሳዊ መሪነት ቦታ መንፈሳዊ ልህቀትን በመሰረታዊነት የሚጠይቅ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ሹመቱ ከአባት ወደ ልጅ የተደረገ የስልጣን ውርስ ነው በማለት እያጣጣሉት እንደሆነ ዘገባዎች ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሞጅታባ ኻሜኒ ብቃት በተግባር ያልተፈተነ በመሆኑ የብዙሃን እምነት ማግኘት የሚያስችል አይደልም ሲሉ ሹመቱን የኮነኑ አሉ።
በአቤል ነዋይ