Fana: At a Speed of Life!

ድሬዳዋ በሕብረ ብሔራዊ አንድነትና አብሮነት አርአያ የምትሆን ከተማ ናት – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ድሬዎች አብሮ ለመኖር ገንዘብ፣ ቋንቋ ወይም እምነት ሳይሆን ሰውነት ይበቃል ብለው የሚያምኑ ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የድሬዳዋ ቆይታቸውን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ÷ የኢንዱስትሪ ከተማ በሆነችው ድሬዳዋ ከ400 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ይህን ከነጻ ንግድ ቀጣናነቷ ጋር በማያያዝ በከተማዋ እየተከፈቱ የሚገኙ የተስማሚነትና ምዘና ፍተሻ ጣቢያዎች ከውጪ የሚገቡና የሚላኩ ምርቶችን ለማሳለጥ በእጅጉ ጠቃሚ ናቸው ብለዋል።

ከጨርቃ ጨርቅ ምርት ባለፈ ለግንባታ ዘርፉ የሚሆኑና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች መጀመራቸውን ጠቅሰው÷ መሰል ሥራዎችን በማጠናከር የድሬዳዋን ገቢ ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ድሬዳዋ በተራሮች የተከበበች ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በአካባቢው ከሚዘንበው ዝናብ የሚነሳው ጎርፍ ተራሮቹን ታክኮ ወደ ከተማዋ እንደሚመጣ አስረድተዋል፡፡

ሊከሰት የሚችልን ጎርፍ ለመከላከልም እርከን መስራት፣ ዛፎችን መትከል እና ቤቶችን በዲዛይን በመገንባት ውሃ የሚፈስበትን ሥርዓት ማበጀት አስፋላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ተራሮቹ የሚያምሩ እንዲሆኑና ሥርዓት ያለው የቤት ግንባታ በመከተል ድሬዳዋን ይበልጥ ውብና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ድሬዎች በምግብ ዝግጅትና ሰዎችን በፍቅር ተቀብሎ በማስተናገድ ጠንካራ እሴት እንዳላቸው ጠቁመው ÷ በሕብረ ብሔራዊ አንድነትና አብሮነት አርአያ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

ድሬዎች አብሮ ለመኖር ገንዘብ፣ ቋንቋ ወይንም እምነት ሳይሆን አብሮ ለመኖር ሰውነት ይበቃል ብለው የሚያምኑ መሆናቸውንም ነው ያወሱት፡፡

በአጠቃላይ በድሬድዋ ከትውልድ ግንባታ፣ ከእርሻ፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከከተማ ልማት፣ ከሕዝብ ለሕዝብ ትስስርና የሚታሰበውን ብልጽግና ከመቀየስ አንጻር ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እንዳሉ መመልከታቸውን አስረድተዋል።

በዮናስ ጌትነት

👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.