Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች የድል ፕላዛና ቁርጡሚ የወንዝ ዳርቻ ልማትን አገልግሎት አስጀመሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የድል ፕላዛ እና ቁርጡሚ የወንዝ ዳርቻ ልማትን ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች÷በቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ እጅግ ዘመናዊ ሆኖ የተገነባውን የድል ፕላዛና የቁርጡሜ የወንዝ ዳርቻ ልማት አጠናቅቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል።

በአንድ ወቅት የወንጀለኞች መሸሸጊያና የቆሻሻ መጣያ የነበረውን ስፍራ ዛሬ ውብ፣ ለአይን ማራኪና የከተማዋ አንዱ የቱሪስት መስህብ አድርገን ገንብተነዋል ነው ያሉት፡፡

የድል ፕላዛ በውስጡ 21 ሺህ 906 ካሬ ሜትር የወለል ስፋት ያለው ፕላዛ፣ በአንድ ጊዜ 500 መኪናዎችን ማቆም የሚችሉ ባለ ሦስት ወለል የመሬት ውስጥ ወለሎች መኪና ማቆሚያን ያካተተ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ዘመናዊ የፓርኪንግ ማኔጅመንት ሥርዓት፣ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል እና የእሳት አደጋ መከላከያ ዘዴ የተገጠመለት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

7 ሄክታር መሬት የሚሸፍን ውብ የአረንጓዴ ስፍራ፣ ምቹ የእግረኛ መንገዶች፣ ዘመናዊና ባህላዊ የስጦታ ዕቃ መሸጫዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች እና ቢሮዎችን እንደያዘም ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል 2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የቁርጥሜ የወንዝ ዳርቻ ልማት የተለያዩ የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎችን፣ የሕፃናትና የአዋቂዎች ስፖርት ማዘውተሪያዎችን አካትቶ በጽዱና በቆንጆ ሁኔታ መገንባቱን ተናግረዋል።

እንዲህም የህፃናት መጫወቻ፣ ⁠የስፓርት ሜዳ፣ አምስት አንፊ ቴአትር ማካተቱን ነው ከንቲባ አዳነች ያስረዱት፡

ስለ ከተሜነት ስናወራ የተሳለጠ መሰረተ ልማት ያለው፣ የሕዝብ የጋራ መገልገያ ስፍራዎች ያሉት፣ የሥራ እድልን የሚፈጥር ንፁህ፣ ውብ፣ ምቹ መኖሪያ እና ጤናማ አካባቢን መፍጠር ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜና በታለመለት የጥራት ደረጃ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.