Fana: At a Speed of Life!

ባለሥልጣኑ በአጥር የተዘጉ ከ1 ሺህ 400 በላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን አስከፈተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን በመዲናዋ በአጥር የተዘጉ 1 ሺህ 434 የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን አስከፈተ፡፡

የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ ሰለሞን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት÷ በመዲናዋ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በአጥር በመዘጋታቸው ምክንያት የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር ቆይቷል፡፡

ባለስልጣኑ በሁሉም ሪጅኖች ባደረገው የዳሰሳ ጥናት 2 ሺህ 438 በሚሆኑ ቦታዎች ላይ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ታጥረው መገኘታቸውን አመልክተዋል፡፡

በዚህም በትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ እያሳደረ ያለውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነዋሪዎች አጥሮችን እንዲያነሱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል ነው ያሉት።

ከሚመለከታቸው የጸጥታና አስተዳደር አካላት ጋር በቅንጅት ላለፉት ሁለት ወራት በተከናወነ የዘመቻ ስራ በ1 ሺህ 434 ቦታዎች ላይ ታጥረው የነበሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እንዲከፈቱ መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ጊዜያት ከ1 ሺህ በላይ በሚሆኑ ቦታዎች ላይ የተዘጉ አጥሮችን የማስከፈት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል፡፡

በሒደቱ ሕብረተሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጉን ጠቅሰው÷ ሙሉ በሙሉ በከተማዋ ውስጥ የታጠሩ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች እስኪከፈቱ ድረስ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.