Fana: At a Speed of Life!

ፒኤስጂ ከቼልሲ – ተጠባቂው ፍልሚያ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ በ16ቱ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ዛሬ ምሽት ፒኤስጂ ከቼልሲ የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡

የአምና የመድረኩ አሸናፊ ፒኤስጂ በዚህ የውድድር ዓመት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በማድረግ 16ቱን መቀላቀሉ ይታወሳል፡፡

የፈረንሳዩ ክለብ ፒኤስጂ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ባሳካበት 2024/25 የውድድር ዓመት 16ቱን የተቀላቀለው በተመሳሳይ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በማድረግ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በዚህ የውድድር ዘመን በተለያዩ ጊዜያት ወሳኝ ተጫዋቾቹን በጉዳት እያጣ የሚገኘው ፒኤስጂ በአንጻራዊነት በአምና ምርጥ ብቃቱ ላይ አይገኝም፡፡

ከአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ባለፈ በፈረንሳይ ሊግም እየተፈተነ የሚገኘው ቡድኑ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ከተከታዩ በአንድ ነጥብ ብቻ በመብለጥ ነው፡፡

ፒኤስጂ የዛሬውን ተጠባቂ ጨዋታ የሚያደርገው በሳምንቱ መጨረሻ በሊጉ በሞናኮ ከደረሰበት ሽንፈት መልስ ነው፡፡

ተጋጣሚው ቼልሲ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ወጥ ብቃት ማሳየት ባይችልም በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ አስቀድመው 16ቱን ከተቀላቀሉ ቡድኖች መካከል አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የቀድሞ የፈረንሳዩ ክለብ ስትራስቡርግ አሰልጣኝ ሊያም ሮሴንየር ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ፈረንሳይ በመመለስ ቼልሲን እየመሩ ፒኤስጂን የሚገጥሙ ይሆናል፡፡

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ከኤፍ ኤ ካፕ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ድል መልስ የሚያደርገው ፍልሚያ ነው፡፡

በ2025 ሁለቱ ቡድኖች በዓለም ክለቦች ዋንጫ ፍጻሜ ላይ ተገናኝተው ቼልሲ በማሸነፍ የዋንጫው ባለቤት መሆኑ አይዘነጋም፡፡

ከ10 ዓመት በፊት በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ መድረክ ሁለቱ ቡድኖች በ16ቱ ጥሎ ማለፍ ተገናኝተው ፒኤስጂ በድምር ውጤት 4 ለ 2 በማሸነፍ ቼልሲን ከውድድሩ ማሰናበቱ ይታወሳል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው እስካሁን በሁሉም ውድድር 10 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን፥ ሁለቱም በተመሳሳይ ሦስት ጊዜ ድል ሲቀናቸው በአራቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ምሽት 5 ሰዓት ላይ በፓርክ ደ ፕሪንስ ስታዲየም የሚጀምረውን የሁለቱ ቡድኖች የ16ቱ ጥሎ ማለፍ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ስፔናዊው ዳኛ አሌሃንድሮ ሄርናንዴዝ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ይሆናል፡፡

በተመሳሳይ ሰዓት ሪያል ማድሪድ በሜዳው ሳንቲያጎ ቤርናባው ማንቼስተር ሲቲን ያስተናግዳል፡፡

ሪያል ማድሪድ በዚህ የውድድር ዓመት 16ቱን የተቀላቀለው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ አድርጎ ሲሆን፥ ማንቼስተር ሲቲ በበኩሉ በቀጥታ 16ቱን መቀላቀሉ አይዘነጋም፡፡

በዚህ የውድድር ዓመት በሊግ ቅርጽ በተደረጉ ጨዋታዎች በመድረኩ 6ኛ ሳምንት ላይ ተገናኝተው ማንቼስተር ሲቲ ማሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡

በማድሪድ በኩል ኪሊያን ምባፔ፣ ሮድሪጎ፣ ቤሊንግሃም፣ ካሬራስ፣ ኤደር ሚሊታኦ፣ ዴቪድ አላባ እና ዳኒ ሴባዮስ የመሳሰሉ ተጫዋቾች በጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ናቸው፡፡

ምሽት 2 ሰዓት ከ45 ላይ ባየር ሊቨርኩሰን ከአርሰናል እንዲሁም ምሽት 5 ሰዓት ላይ ቦዶ ግሊምት ከስፖርቲንግ ሊዝበን ሌሎች ዛሬ ምሽት የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.