Fana: At a Speed of Life!

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የመኖሪያ ቤት አስረከቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለሀገር ባለውለታ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት አስረክበዋል።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ዛሬ በልደታ ክፍለ ከተማ የገነባነውን ዘመናዊ የጂ+4 የመኖሪያ ህንፃ፣ ለማሕበራዊ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለሀገር ባለውለታ ለሆኑ ነዋሪዎቻችን “ቤት ለእምቦሳ” ብለን በክብር አስረክበናል ብለዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ የልማት ስራዎች የተነሱ በቀበሌ ቤት ውስጥ በደባልነት፣ በጥገኝነትና በላስቲክ ቤት ውስጥ እና የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በላያቸው እያለፈ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለነበሩ ወገኖቻችን ጭምር ቤት አስረክበናል ሲሉም ገልጸዋል።

አዲስ አበባ በሰው ተኮር ስራዎቿ ተምሳሌት ሆናለች ያሉት ከንቲባዋ÷ ሰው ተኮር ስራዎችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጀምረው በርትተን እንድንሰራ የስራ መመሪያ ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ላለፋት 7 ዓመታት በሰው ተኮር እሳቤያችንና በበጎነት አገልግሎት ተሳትፎ ከ45 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች መገንባት ችለናል ብለዋል።

በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር በ4 ወራት ጊዜ ውስጥ የተገነባው የመኖሪያ ቤቱ÷ 5 ነባር ቤቶችን በማንሳት 70 አባወራዎችን ቤት እንዲገኙ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህም ከእጦት መንፈስ ወጥተን ቦታን በአግባቡ በመጠቀም ትልቅ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የሚያሳይ ሲሆን በከፍተኛ የጥራት ደረጃ ተገንብቷል ነው ያሉት።

ግንባታው የጥራት ደረጃውን የጠበቀ፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ፣ የዜጎችን ክብር የሚመጥንና የቤት ቁሳቁስ የተሟላለት ዘመናዊ ህንፃ መሆኑን ገልጸው÷ ከተማችን ለሁላችንም ትበቃለች፤ መተሳሰብና ፍቅር ካለ ደግሞ ይበልጥ መስራት ይቻላል ብለዋል።

በቀጣይም ለብዙዎች ለመድረስ በትጋት እንሰራለን ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ ይህን እጅግ ዘመናዊና የዜጎችን ክብር የሚመጥን የመኖሪያ ቤት ግንባታ በማስተባበር ለተሳተፉ ተቋማት፣ ባለሀብቶችን ላስተባበሩ የከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ፣ ለደገፉ ባለሀብቶችና ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.