በሳምንት 1 ሚሊየን ዜጎች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እየተመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሳምንት 1 ሚሊየን ዜጎች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ እየተመዘገቡ ነው አለ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም፡፡
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላትና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳመለከቱት፤ እስካሁን ድረስ 38 ሚሊየን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ወስደዋል፡፡
የባንክ ደንበኞች የሂሳብ ቁጥራቸውን ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር እንዲያስተሳስሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የምዝገባ ሂደቱ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ሁሉም ባንኮች ደንበኞቻቸው በቅርንጫፎች እና በኦንላይን አገልግሎት የባንክ ሂሳብ ቁጥራቸውን ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር እንዲያስተሳስሩ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ፋይዳ መታወቂያ ለባንኮች ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ ባንኮች 2 ሺህ የመመዝገቢያ ማሽኖችን ገዝተው እየመዘገቡ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
በባንኮች እና በሌሎች ተቋማት የ80 ሚሊየን ደንበኞችን መረጃ የማረጋገጥ ስራ መከናወኑን ጠቁመው፤ ባንኮች ብቻ በቀን የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ደንበኞችን መረጃ እያረጋገጡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ ምዝገባው በባንኮች፣ በኢትዮ ቴሌኮም እና በኢትዮ ፖስታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
5 ሺህ የምዝገባ ማሽኖች በሁሉም አካባቢዎች መኖራቸውን ገልጸው በቅርቡ ተጨማሪ 3 ሺህ ማሽኖች ወደ ምዝገባ ይገባሉ ብለዋል፡፡
በቅርቡ በሱፐር አፕ ኤጀንት በኩል በገጠር አካባቢዎች የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባ እንደሚጀመር አመልክተዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ