ቦርዱ ምርጫ የሚደረግባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚደረግባቸው አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።
በውይይቱ ወቅት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ እንዳሉት፤ ቦርዱ በራሱ የደረሰባቸውንና የእርምት ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ያላቸው ጉዳዮችን የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማስተካከያ እንዲያደርጉ የራሱን ጥረት እያደረገ ነው።
አሁንም ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለይተው ለቦርዱ ባሳወቋቸው አካባቢዎች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ አካላትን የሚያሳትፍ የክትትልና ቁጥጥር ኮሚቴ እንደሚያሠማራ አረጋግጠዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች የስራ እንቅስቃሴ እና የፖለቲካ ምኅዳር ሁኔታን በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ቀደም ሲል የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችና የከተማ መስተዳድር ከንቲባዎች፣ የፌደራልና የክልል የፀጥታ ተቋማት አመራሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት ቦርዱ በአረንጓዴ፣ በቢጫና በቀይ የተፈረጀ የፀጥታ ሁኔታ መረጃ ቀርቦ ውይይት መደረጉ ይታወቃል።