አቢሲኒያ ባንክና ቪዛ ዲጂታል ክፍያዎችን ማፋጠን የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአቢሲኒያ ባንክ እና ቪዛ በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያዎችን ማፋጠን የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂካዊ የአጋርነት ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የፋይናንስ አካታችነትን እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ተደራሽነትን እንደሚያጠናክር ተመላክቷል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በሀገሪቱ አካታችና ፈጠራ የታከለበት የዲጂታል ክፍያ መፍትሔዎችን ለማስፋፋት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያረጋግጥም ተገልጿል።
የባንኩ ቺፍ ዲጂታል ባንኪንግ ኦፊሰር ወ/ሮ ሶስና መንገሻ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ስምምነቱ የዲጂታል ባንክ አገልግሎቶችን በማሳደግ ደህንነቱ የተጠበቀና አዳዲስ የክፍያ መፍትሄዎችን የማቅረብ አቅምን ያሳድጋል፡፡
አጋርነቱ የክፍያ ሥርዓቶችን ለማዘመን፣ የጥሬ ገንዘብ አልባ ግብይቶችን ለማስተዋወቅ እና እንከን የለሽ የዲጂታል ግብይትን ለማጠናከር እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡
ቪዛ እና የአቢሲንያ ባንክ አዳዲስ አቅሞችን ለማስተዋወቅ፣ የክፍያ መሠረተ ልማቶችን ለማጠናከር እና የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገት ለመደገፍ በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።
በቪዛ የምስራቅ አፍሪካ ክላስተር ኃላፊ ያሬድ እንዳለ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ገበያ በፍጥነት በማደግ ላይ በመሆኑ ተቋሙ የዲጂታል ክፍያ ምህዳሩን እድገት ለመደገፍ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
ከአቢሲንያ ባንክ ጋር ያለን ዘላቂ ትብብር ፈጠራን እና የፋይናንስ አካታችነትን በመደገፍ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣን እና ምቹ ክፍያዎችን በማስቻል የጋራ ራዕይን ያንጸባርቃል ነው ያሉት፡፡
በዚህ አጋርነት የአቢሲንያ ባንክ የቪዛን ዓለም አቀፍ የክፍያ ኔትወርክ፣ ቴክኖሎጂ እና የባለሙያ እውቀትን በመጠቀም በፕሪሚየም ዴቢት ምርቶች ላይ ኢንቨስት ማድረጉን እና የዲጂታል ባንክ አቅርቦቱን እንደሚያጠናክር ጠቅሰዋል።
ትብብሩ ደህንነቱ የተጠበቀ የክፍያ ተቀባይነት እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የክፍያ አቅም እንዲስፋፋና የሀገሪቱን ሸማቾች እና ነጋዴዎች በዓለም አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲሳተፉ እንደሚረዳም ተጠቁሟል።
በአድማሱ አራጋው