Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ባንክ አጠቃላይ ሃብት 52 ነጥብ 76 ቢሊየን ብር ደረሰ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ባንክ አጠቃላይ ሀብት 52 ነጥብ 76 ቢሊየን ብር ደረሰ፡፡

የአማራ ባንክ ባወጣው መግለጫ÷ በፋይናንስ ዘርፉ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማስጠበቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል፡፡

አማራ ባንክ በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት 1 ነጥብ 82 ቢሊየን ብር ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን÷ አጠቃላይ ሀብቱንም 52 ነጥብ 76 ቢሊየን ብር አድርሷል፡፡

የአማራ ባንክ በፋይናንስ የተረጋጋ፣ ጤናማ አሰራር የዘረጋ፣ ብሔራዊ ባንክ ያወጣቸውን የቁጥጥር መመሪያዎች በጥብቅ የሚከተልና የሚያከብር መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

ባንኩ የቀን ከቀን ሥራውን የባንክ ቢዝነስ አሰራር መርሆዎችንና መመሪያዎችን በመከተል እያከናወነ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

አማራ ባንክ ጠንካራ የአስተዳደር ሥርዓት በመገንባትና በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዙሪያ ግልጸኝነት ያለው አሰራር በማስፈን ረገድ በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

አማራ ባንክ የብድር ፖርትፎሊዮና የክሬዲት ተጋላጭነቱን አስመልክቶ ሙሉ በሙሉ በብሔራዊ ባንክ በተላለፉ የጥንቃቄ መመሪያዎች ገደብ ውስጥ ሆኖ በመፈፀም ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

የአማራ ባንክ ለአንድ ተበዳሪ የሚሰጠው ጠቅላላ የብድር መጠን ብሄራዊ ባንክ ከፈቀደው የቁጥጥር ገደብ የ25 በመቶ በታች ሲሆን ÷ ይህም የብሔራዊ ባንክን የአደጋ ስጋት መመሪያዎችን በመከተል የተፈጸመ መሆኑ ተጠቅሷል።

አማራ ባንክ አሁናዊ ቁመናው በፋይናንስ የተረጋጋ፣ ጤናማ አሰራር የዘረጋና በረጅም ጊዜ እድገት ላይ አተኩሮ እየሰራ ያለ ተቋም መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

አማራ ባንክ ራሱን ለማጠናከርና ለኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እድገት ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ለማበርከት ከተቆጣጣሪዎች፣ ባለአክሲዮኖችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጥል አረጋግጧል፡፡

በቅርቡ በአንዳንድ ሚዲያዎች የተሰራጩ ዘገባዎች የባንኩን የአሁናዊ ሁኔታ ያላሳዩ፣ የመደበኛ አገልግሎትና የፋይናንስ አሰራር ሁኔታን በአግባቡ ያልተገነዘቡ፣ ደንበኞችን የማይመጥኑና የተሳሳቱ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡

አማራ ባንክ ጉዳዩን አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ ሙሉ ቃል ሊንኩን በመጫን ያንብቡ፡-https://shorturl.at/jZM2Y

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.