መሶብ ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት በአንድ ቦታ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት በአንድ ቦታ እንዲያገኙ እያስቻለ ነው አሉ የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ።
በኦሮሚያ ክልል ማያ ከተማ አስተዳደር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ ጀምራል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት አቶ ከፍያለው ተፈራ እንዳሉት÷ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች የሚገባቸውን አገልግሎት በአንድ ቦታ እንዲያገኙ እያስቻለ ይገኛል።
ለሕብረተሰቡ የቅሬታ ምንጭ የነበረውን የአግልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የማያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢፍራህ ወዚር (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመውን እንግልት እንደሚያስቀርና የአገልግሎት አሰጣጡን እንደሚያቀላጥፍ ገልጸዋል።
በማዕከሉ 4 የፌዴራል እና 23 የከተማ አስተዳደር ተቋማትን በማካተት በ12 መስኮት አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
በምንያህል መለሰ