7 የተፈጥሮ ሐይቆቿን ከኮሪደር ልማት ጋር ያስተሳሰረችው ቢሾፍቱ…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቢሾፍቱ ከተማን የቱሪስት መዳረሻነት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው አሉ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ፡፡
ከንቲባ አለማየሁ እንዳሉት÷ ተፈጥሮ ያደላት ቢሾፍቱ ሰባት የተፈጥሮ ሐይቆችን በውስጧ የያዘች ብቸኛ የኢትዮጵያ ከተማ ናት፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ተሰባጥረው የሚገኙት እነዚህ ሐይቆች ለከተማዋ ልዩ ውበት ከማጎናጸፍ ባለፈ የቱሪስት መዳረሻነቷን ይበልጥ እያጠናከሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን ዘመናዊ ፣ ውብ፣ ምቹ እና ጽዱ እያደረጋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በከተማዋ 104 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለማከናወን ታቅዶ እስካሁን 87 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የቢሾፍቱ ኮሪደር ልማት ሥራ ከተፈጥሮ ጋር በልዩ ሁኔታ የተሳሰረ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ከንቲባው÷ ይህም ከተማዋን ይበልጥ ውብና ምቹ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አመልክተዋል፡፡
በተለይም የኮሪደር ልማት ሥራውን ከተፈጥሮ ሐይቆች ጋር በማሰናሰል እየተሰራ ያለው ሥራ ከተማዋን ልዩ ገጽታ በማላበስ የቱሪስት መዳረሻነቷን ያሳድጋል ነው ያሉት፡፡
በተፈጥሮ የታደለችው ቢሾፍቱ ከሐይቆች በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ ተራራማና ከፍተኛ ቦታዎች እንዲሁም ያላት ተስማሚ አየር የቱሪስት መዳረሻነቷን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አውስተዋል፡፡
በሚቀትሉት ዓመታት ቢሾፍቱ በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ እንድትሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የከተማዋን የኮንፈረንስ ማዕከልነት ይበልጥ ለማጠናከርም ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ፓርኮችና ሌሎች የመዝናኛ ሥፍራዎች እየተገነቡ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
የተፈጥሮ ሐይቆችን በማስዋብና በማልማት ጎብኚዎች አይረሴ ጊዜ እንዲያሳልፉ ለማስቻል በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በቅርቡ ግንባታው የተጀመረው ግዙፉ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ለከተማዋ ቀጣይ ድምቀትና መጻኢ እድል ከፍተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ የሚገኙ 1 ሺህ 978 አምራች ኢንዱስትሪዎች በከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች መሰማራታቸውን አስረድተዋል፡፡
ቢሾፍቱ የለውጡ መንግሥት አዳዲስ ኢኒሼትቮች በተግባር የተገለጡባት ከተማ ናት ያሉት ከንቲባው÷ ለአብነትም በሌማት ትሩፋትና ኮሪደር ልማት ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡
63 ሺህ ሄክታር ላይ ያረፈችው ቢሾፍቱ ከተማ በሶስት ክፍለ ከተሞች እና በ11 ወረዳዎች የተዋቀረች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ