የኩዌት መንግሥት በጋሞ ዞን በደረሰው አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ሐዘን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኩዌት መንግሥት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ሐዘን ገልጿል፡፡
የኩዌት ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ መንግሥት ባስተላለፈው የሐዘን መግለጫ መልዕክት÷ ለኢፌዲሪ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ለተጎጂ ቤተሰቦች የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ በተከሰተው አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ያለውን አጋርነት ገልጾ÷ ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡
በጋሞ ዞን የካቲት 30 እና መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍና የመሬት ናዳ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
በተከሰተው አደጋም እስከ ትናንትናው ዕለት ድረስ የ81 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጋሞ ዞን መረጃ አመልክቷል፡፡