Fana: At a Speed of Life!

ነዳጅን በኃላፊነት ለመጠቀም የሚያስችሉ አሰራሮች በአግባቡ እንዲተገበሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በመካከለኛው ምሥራቅ ከተፈጠረው ቀውስ ጋር በተገናኘ ነዳጅን በኃላፊነት ለመጠቀም የሚያስችሉ አሰራሮች በአግባቡ እንዲተገበሩ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ነዳጅን በቁጠባና ለመሠረታዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም የኤሌክትሪክ መኪናዎችንና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በአግባቡ መጠቀም፣ የአነዳድ ባህል ለውጥ ማድረግ እንዲሁም ለጥራት ቁጥጥርና የአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ ጫና ለመቋቋምና የሀገርን ኢኮኖሚ በዘላቂነት ለመታደግ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በመንግስትና በግል ተቋማት ተግባራዊ መደረግ ያለባቸውን አሰራሮች አመላክቷል፡፡

በነዳጅና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ነዳጅን በመተው የኤሌክትሪክ ኃይልን ብቻ እንዲጠቀሙና በነዳጅ የሚሰሩትን ወደ ኤሌክትሪክና ተፈጥሮ ጋዝ የመቀየር ስራን ማጠናከር እንደሚገባ ሚኒስቴሩ አስገንዝቧል፡፡

በተጨማሪም እስከ 20 ቶን የሚጭኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ከ20 ቶን በላይ የሚጭኑ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ወደ ተፈጥሮ ጋዝና ኤሌክትሪክ እንዲቀየሩ በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡

በክልልና በፌዴራል ደረጃ ያሉ ሁሉም የመንግስትና የፕሮጀክት ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ እንዲዞሩ በማድረግ የተጀመረውን ሀገራዊ እቅድ ወደ ተሟላ ትግበራ ማሸጋገር ይጠበቃል ነው ያለው፡፡

ህብረተሰቡ አውቶብስ፣ ባቡርና ሌሎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በስፋት እንዲጠቀምና በወጣው ታሪፍና መርሐ ግብር አገልግሎቱ ያለ መቆራረጥ እንዲሰጥ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡

ከአንድ ቤት ውስጥ ብዙ መኪናዎችን ለየብቻ ይዞ ከመውጣት ይልቅ በጋራ መጠቀም እንደሚገባ ገልጾ፥ በከተማ ውስጥ የሚደረጉ አጫጭር ጉዞዎችን በእግርና በብስክሌት የማድረግ ባህልን ማዳበር እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡

ነዳጅንና የካርቦን ልቀትን የሚቀንስ፣ ከሞገደኝነት የጸዳ አነዳድን ተግባራዊ ማድረግና ወቅታዊ የመኪና ጥገናን ማጠናከር እንዲሁም ኦሪጅናል መለዋወጫዎችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡

የጭስ ልኬት መመሪያን በተሟላ ሁኔታ መተግበርና ሁሉም ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ ስታንዳርድ የጸደቁ የነዳጅና ጭስ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡

የቀረበው ሀገራዊ ጥሪ የሀገርን የውጭ ምንዛሪ ለማዳን፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና ዜጎች በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ እንዳይጎዱ ለማድረግ የታለመ መሆኑንም ሚኒስቴሩ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.