በአቶ አህመድ ሺዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ከጣሊያን የማቴ ዕቅድ ከፍተኛ ልዑካን ጋር ተወያየ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ከጣሊያን የማቴ ዕቅድ ከፍተኛ ልዑካን ጋር በመሰረተ ልማት ግንባታ ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡
ውይይቱ በኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲሁም በግዙፉ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ዙሪያ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ፕሮጀክቶቱ የኢትዮጵያን የኃይል አማራጭ እንዲሁም የአቪዬሽን መሰረተ ልማትን በማሳደግ የሀገሪቱን ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት እንደሚያግዙ ተመላክቷል፡፡
በዚህም ጣሊያን በማቴ ዕቅድ ስር የተለያዩ የገንዘብ አማራጮችን በመፍጠር በኢትዮጵያ የሕዝብ መሰረተ ልማቶችን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗ ነው የተነገረው፡፡
በውይይቱ ጣሊያን በሁለቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርግበት ሁኔታ ላይ አጽንኦት የተሰጠ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ ልዑክ ፕሮጀክቶቹ የኢትዮጵያን ዘላቂ እድገት ከመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
የማቴ ዕቅድ በጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ በፈረንጆቹ 2024 ይፋ የተደረገ ኢኒሼቲቭ ሲሆን በአፍሪካ ጣሊያን ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ተጠቁሟል።
ኢኒሼቲቩ የአውሮፓ ሕብረት በአፍሪካ ካለው ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም ሆኖ በኃይል፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና እና ህገወጥ ስደትን በሚያስቆም ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ ነው።