በየቀኑ ቢሊየን ዶላሮች እየፈሰሰ የሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በየቀኑ ቢሊየን ዶላሮች እየፈሰሰ 19ኛውን ቀን የያዘው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት እያደረሰ የሚገኘው ኪሳራ እያሻቀበ ይገኛል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በፈጸሙት የጋራ የአየር ድብደባ የተጀመረውና ወደ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የተለወጠው ይህ ጦርነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ከነበሩት በጣም ውድ ጦርነቶች መካከል አንዱ ሆኗል።
ጦርነቱ አንደኛ ወሩን እንኳን ሳይደፍን ኢኮኖሚያዊ ጥላውን እያጠላ ሲሆን በመንግሥታት፣ በገበያ፣ በሸማቾች እና በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖውን እያሳደረ ይገኛል።
ከመሰረተ ልማትና ሰብዓዊ ጉዳት ባለፈ በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተጽዕኖ እያሳደረ የሚገኘው ይህ ጦርነት÷ ከአካባቢው ርቀው የሚገኙ ሰዎችም የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።
የዋጋ ግሽበት፣ የአቅርቦት ሰንሰለት መስተጓጎል እና የግብርና፣ የጉዞና የንግድ እንቅስቃሴ እንደነበረ አለመሆኑ ከአሁኑ በርካታ ሀገራት ውጥረት ውስጥ ገብተዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የተዘጋውና የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፈው የሆርሙዝ ሰርጥ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደርና ግሽበትን በማስከተል የተለያዩ የዓለም ሀገራት ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀሙና አዳዲስ ርምጃዎች እንዲወስዱ በማስገደድ ላይ ይገኛል።
በተለይም በቀጥታ ውጊያው ላይ እየሳተፉ የሚገኙ ሀገራት ለሚምዘገዘጉ የጦር መሳሪያዎች፣ ለሎጂስቲክስ እንዲሁም የባሕር ኃይል እንቅስቃሴ ጥቃቶችን ለማምከን በየደቂቃቅ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ በማፍሰስ ላይ ናቸው።
የዓለም ልዕለ ኃያሏ ሀገር አሜሪካ ለጦርነቱ ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ ያወጣች ሲሆን÷ ጦርነቱ በተጀመረ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ቀናት ብቻ ከ11 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ማድረጓ ተዘግቧል።
የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል (CSIS) ባወጣው መረጃ አሜሪካ ባለፉት 12 ቀናት ከ16 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ማውጣቷን አመላክቷል።
እንዲሁም የጦርነቱ ሌላኛዋ ተሳታፊ እስራኤልም በኢራን ላይ ለምትፈጽማቸው ጥቃቶች እንዲሁም ጥቃቶችን ለመከላከል ከፍተኛ ወጪ እያወጣች ትገኛለች።
በዚህም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ የመከላከያ ወጪዎቿን ለማመጣጠን ሀገራዊ በጀቷን በድጋሚ ያዋቀረች ሲሆን÷ በዚህም ወደ 10 ነጥብ 3 ቢሊየን ዶላር ከፍ ማድረጓን የሮይተርስ ዘገባ ያሳያል።
የኢራን ድሮኖች እና ሚሳኤሎች በየቀኑ በእስራኤል ውስጥ እያንዣበቧት የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ማድረግ አዳጋች እየሆነ መጥቷል፤ ሸማቾች እንደልብ እየተንቀሳቀሱ አይደለም፤ የንግድ እንቅስቃሴዋም በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ መጥቷል።
በኢራን በኩል ደግሞ በተቃራኒው ከተሰለፉት ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ወጪዋ ዝቅተኛ ቢሆንም በመሠረተ ልማት ላይ እንዲሁም በሰዎች ላይ እየደረሰ የሚገኘው ጉዳት ከፍተኛ ነው።
በዚህም አስካሁን ከ1 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ሲሞቱ 3 ነጥብ 2 ሚሊየን ኢራናውያን ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ።
እንዲሁም ኢራን በየቀኑ ወደ ውጪ ትልክ የነበረው 3 ነጥብ 3 ሚሊየን በርሜል ነዳጅ መቆሙ ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያስከተለባት እንደሚገኝ የብሉምበርግ መረጃ ያሳያል።
በጦርነቱ ጎራ ከፍለው ጦር ከሚወራወሩት ሀገራት ባለፈ በሌሎች ሀገራትም ሰፊ የኢኮኖሚ ተጽዕኖ እያሳደረ ሲሆን÷ በሆርሙዝ ሰርጥ የንግድ እንቅስቃሴ መስተጓጎል በነዳጅ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተጽዕኖ በማሳደር እያንዳንዱን የዓለምን ሕዝብ በር እያንኳካ ይገኛል።
የትራንስፖርትና የሸቀጥ ዕቃዎች ዋጋ መናር የዋጋ ግሽበትን በመጋበዝ ላይ ይገኛል። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የነዳጅ ዋጋ በዚህ ልክ እየጨመረ ከቀጠለ የሀገራት ኢኮኖሚ እድገትን ከማዘግየት ባለፈ ጦርነቱ ቀጥተኛ ያልሆነ ጫና እያሳደረ ይመጣል።
ይህ ጦርነት መቋጫውን ካላገኘ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ተፅዕኖዎች ማስከተሉ አይቀሬ መሆኑን፣ የኢንቨስትመንትና የእድገት እንቅስቃሴ መቀዛቀዝም እንደሚከተል ባለሙያዎቹ ያስጠነቅቃሉ።
በዮናስ ጌትነት