Fana: At a Speed of Life!

የሙስና ወንጀሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ከ53 ቢሊየን ብር በላይ ማስመለስ ተችሏል – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሙስና ወንጀሎች የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ከ53 ቢሊየን ብር በላይ ማስመለስ ተችሏል አሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል፡፡

ፖሊስ የሙስና ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር ሙሰኞችን ለፍትህ በማቅረብ ያከናወናቸውን ተግባራት ከስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጋር በዛሬው ዕለት ገምግሟል።

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በወቅቱ እንዳሉት፤ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ በተደረገ ጠንካራ ኦፕሬሽን ከፍተኛ የሆነ የሀገርና የሕዝብ ሀብት በሙስና የመዘበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በዚህም ከ53 ቢሊየን ብር በላይ ማስመለስ መቻሉን ገልጸው፤ ከሪፎርሙ በፊት በነበሩ ዓመታት ከተመዘገበው ሁለት ቢሊየን ብር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ አለው ነው ያሉት፡፡

የሙስና ወንጀሎችን የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር በሪፎርሙ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አስታውሰዋል፡፡

ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም የምርመራ ሥራው ግልፀኝነት የሰፈነበትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሙስናን በመከላከል ጥረት ህብረተሰቡ በሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት፣ በEFP App መተግበሪያ እና በ991 ነፃ የስልክ ጥሪ ጥቆማ በመስጠት በተመዘገበው ስኬት ላይ የነበረው ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከልና የምርመራ ሥራን ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያከናውነው ተግባር እንደ ሀገር የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.