Fana: At a Speed of Life!

የኮሪደር ልማት ከተማን ከማዘመን ባለፈ ጉልህ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያስገኘ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮሪደር ልማት ከተማን ውብ፣ ለኑሮ ምቹና ዘመናዊ ከማድረግ ባለፈ ጉልህ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ እያስገኘ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ከተማ፣ ከተሜነት፣ ክትመት እና የኮሪደር ልማት በሚል መሪ ሐሳብ ከቃና ቲቪ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ ነጠላ ግብ ፣ድርብ ግብ እንዲሁም ድርብርብ ግብ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

የኮሪደር ልማት በነጠላ ዓላማ የሚሰራ፣ ለነጠላ ጥቅም የሚውል እንዲሁም ነጠላ ፕሮጀክት አለመሆኑን ገልጸው÷ በውስጡ ብዙ ነገሮችን ያሳካ እንደሆነና ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና አካባቢያዊ ግቦች መያዙን አመልክተዋል።

ግቦቹን በዝርዝር ማየት ለሚችል ሰው የኮሪደር ልማት ምን ያህል ድርብርብ ዓላማዎችን ይዞ እንደተነሳ ይገነዘባል ነው ያሉት፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት የሆነውን ሥራ አጥነት ከመቅረፍ አንጻር ኮሪደር ልማት እየተሰራም ሆነ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም ዘርፈ ብዙ ክህሎትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቅሰው÷ የአዲስ አበባ ኮሪደር ወጣቶች ዩኒቨርሲቲ ገብተው ከሚያገኙት እውቀት የላቀ ክህሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን አስረድተዋል።

በዚህም ወጣቶች አዲስ አበባ ላይ ከሰሩ በኋላ በተለያዩ የክልል ከተሞች ሙሉ በሙሉ ዲዛይን ሰርተው የሚያደርጉት ግንባታ መልሶ የሚያስደምም ሆኗል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል በብዙ ሺህ የተገነቡና በአጭር ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁ የቤቶች ግንባታ ሥራ የኮሪደር ልማት አካል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ሕንጻዎች ከኮሪደር ልማት በኋላና በፊት ያላቸው ዋጋ ላይ ልዩነት በመፍጠር ሰዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ ማገዙን ጠቁመዋል።

የኮሪደር ልማት መንገዶችን ምቹ በማድረግ ሰዎች ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ በፍጥነት እንዲደርሱ የበኩሉን ሚና መጫወቱንም አውስተዋል፡፡

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.