የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራችን ለብዙ ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ የተከናወነው የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራ ለብዙ ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ከተማ፣ ከተሜነት፣ ክትመት እና የኮሪደር ልማት በሚል መሪ ሐሳብ ከቃና ቲቪ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸውም የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በጣም ከሚያኮሩ የኢትዮጵያ ሥራዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማት ልጆቻችን የሚኮሩበት ሥራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሥራው ግን በጣም ፈታኝ እንደነበር አስገንዝበዋል፡፡
ማሕበረሰቡ ትስስር እንዲኖረው የጋራ መዝናኛ እና መገናኛ ቦታ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው÷ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራ ለዚህ እሳቤ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ቦታዎችን በአግባቡ በመጠቀም ፓርኮችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ይህም ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚያግዝ አመልክተዋል፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራው በቢሾፍቱ፣ ጅማ፣ አርባ ምንጭ እና ባሕርዳር ከተሞች ላይ በስፋት መሰራቱን ጠቁመው÷ ሀዋሳ ከተማ ላይ ሥራው መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ዲጂታል ቴክኖሎጂ ከዋና ዋና አምስት ግቦቻችን መካከል አንዱ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ሁሉንም ግቦች የሚያስተሳስር ሥርዓት ነው ብለዋል፡፡
የዲጂታል መሰረተ ልማት ባላደገባቸው ሀገራት ትምህርት፣ ጤና እንዲሁም ኢንዱስትሪን የመሳሰሉ ነገሮች ሊሻሻሉ እና ሊያድጉ እንደማይችሉ አስረድተዋል፡፡
ቴክኖሎጂ ውትድርና፣ ትምህርት፣ ትራንስፖርት እና ጤናን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፎችን እንደሚነካ ጠቁመው÷ የእድገት ጽንሰ ሐሳብ ቴክኖሎጂ ከሌለ የተሟላ እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂ ልጆቻችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳደሪ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የቴሌኮም መሰረት ልማት ላይ በርካታ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በአፍሪካ ቀዳሚ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም መገንባቱን አንስተው÷ ዩኒቨርሲቲውም በግንባታ ላይ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በ5 ሚሊየን ኮደርስ ፕሮግራም ስልጠና እስካሁን ድረስ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ስልጠና ማጠናቀቃቸውን አስታውሰዋል፡፡
ቴክኖሎጂ እንደ ሀገር ጥሩ የኢኮኖሚ ዕድገት ለውጥ እያመጣ ነው÷ ይሁን እንጂ በቀጣይ በትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ