ከ41 ሺህ በላይ ሰዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሙዚቃ ውድድር ለመሳተፍ ተመዝግበዋል – የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 41 ሺህ 394 ሰዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት የሙዚቃ ውድድር ለመሳተፍ ተመዝግበው እስካሁን 655 ሰዎች ስራዎቻቸውን አቅርበዋል አለ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት።
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በትብብር ባዘጋጁት የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሙዚቃ ውድድር ተወዳዳሪዎች ስራዎቻቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።
የኢንስቲትዩቱ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተስፋዬ ዘውዴ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ ተወዳዳሪዎች የ1 ሚሊየን ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል።
አሁን ላይ እየተካሄደ ያለው ምዝገባ የመጀመሪያው ዙር መሆኑን ገልጸው÷ በቀጣይም መሰል የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ውድድሮች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
በዚህም የሙዚቃ ውድድሩ ተወዳዳሪዎች ያላቸውን አቅም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ታግዘው ለአድማጭና ተመልካቾች የሚያቀርቡበት ዕድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ዳኞች ተወዳዳሪዎች ያቀረቡትን ስራዎች ፍትሃዊ የሆኑ መመዘኛ መስፈርቶችን ተከትለው በመገምገም አሸናፊዎች እንደሚለዩ አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ በኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ እንዲያድግና ጥልቅ የሆኑ የሳይንሳዊ ምርምር ስራዎችን በመስራት የሕብረተሰቡን ችግር በቴክኖሎጂ ለመፍታት ግብ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ በፈረንጆቹ 2030 የአፍሪካ ግንባር ቀደም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ማዕከል ለመሆን ራዕይ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።