የኮሪደር ልማት ሥራ የዜጎችን ሁለንተናዊ የአኗኗር ዘዬ አሻሽሏል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማት ሥራ የዜጎችን ሁለንተናዊ የአኗኗር ዘዬ በማሻሻል ዘመናዊነትን እያጠናከረ ነው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) “ከተማ፣ ከተሜነት፣ ክትመት እና የኮሪደር ልማት በሚል መሪ ሐሳብ ከቃና ቲቪ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በቆይታቸው በሰጡት ማብራሪያም በኢትዮጵያ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ በርካታ ነገሮችን ጠቅልሎ የያዘ ነው ብለዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ሥራ ዘርፈ ብዙ ግቦች አሉት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን አብራርተዋል፡፡
ስማርት የትራንስፖርት ሥርዓት መዘርጋት እና የአገልግሎት ተቋማትን ማዘመን የኮሪደር ልማት ሥራ ዋነኛ ዓላማ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ከኮሪደር ልማት በፊት በመዲናዋ የተሽከርካሪ መንገድ ለመኪና፣ ለእግረኛ እና ለፓርኪንግ ጭምር ያገለግል እንደነበር አስታውሰው÷ ይህ ደግሞ ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት ለመኪና፣ ለእግረኞች ፣ ለሳይክል እና ለፓርኪንግ አገልግሎት የሚውል ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
ስማርት ትራንስፖርት የኮሪደር ልማት ግብ እና ፍላጎት መሆኑን ጠቁመው÷ ውጤት እየተገኘበት ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
የትራንስፖርት ሥርዓቱ ብዙ ሰዓት ሊፈጅብን አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ አጠቃቀማችንን እያሳደግን ከሄድን ይበልጥ ውጤታማ እንሆናለን ብለዋል፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ የወንዝ ዳርቻ ቦታዎችን ለኑሮ ምቹ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማት ጤናማ ሕብረተሰብ መፍጠሪያ መንገድ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያስገነዘቡት፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በርካታ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በማቅረብ የተሳለጠ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
ሰው ጉዳይ ቢገጥመው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሳይሄድ የገጠመውን ነገር ለፖሊስ ማሳወቅ እንዲችል ለማድረግ ስማርት ፖሊስ ጣቢያ መገንባቱንም አንስተዋል፡፡
ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀም ብዙ ነገሮችን መቀየር እንደሚቻል ገልጸው÷ ከዚህ ቀደም በመዲናዋ በየቦታው በወረቀት የሚለጣጠፉ ነገሮች የቀነሱት ስክሪን መጠቀም በመጀመራችን ነው ብለዋል፡፡
መሰረተ ልማቶችን በጋራ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው÷ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ