4 ሚሊየን ሴቶችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት የማድረግ የሳምንት ዕቅድ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ 4 ሚሊየን ሴቶችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ነው አለ፡፡
‘መጋቢትን ላንቺ’ በሚል መሪ ሀሳብ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ሴቶችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት የሚያደርግ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ እየተካሄደ ይገኛል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላትና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሳሚናስ ሰይፉ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንዳሉት፤ በንቅናቄው 4 ሚሊየን ሴቶችን ለመመዝገብ ታቅዷል።
ሴቶች በነቂስ ወጥተው ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መመዝገብ መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ ከተጀመረ እስካሁን ድረስ 39 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ለፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የተመዘገቡ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 42 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ብለዋል።
ሴቶችን የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ማድረግ የሴቶች መብትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የጎላ አበርክቶ ያለው በመሆኑ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እየተሰራበት ነው ብለዋል።
በመሳፍንት እያዩ