ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ታዳሽ ኃይልን በስፋት ማምረትና መጠቀም ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከነዳጅ ጋር በተያያዘ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ታዳሽ ኃይልን በስፋት ማምረትና መጠቀም ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከተማ፣ ከተሜነት፣ ክትመት እና የኮሪደር ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ ከቃና ቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከጥቂት አመታት በፊት የኤሌክትሪክ መኪና መጠቀም አለብን በሚል ስናነሳ አንዳንዶች ሲያጉረመርሙ ተስተውሏል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች ሀገር ባለመሆኗ አማራጭ የኃይል አጠቃቀም ስልት መከተል እንዳለባት አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ እንደተከሰተው ዓይነት ጦርነት ችግር ሲያጋጥም የነዳጅ አቅርቦት እንደሚስተጓጎል አንስተዋል።
በጦርነት ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ ሲጨምር ችግሩ ከባድ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ዘላቂ መፍትሄው ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልን በስፋት ማምረት ስለምትችል የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ መጠቀም አዋጭ ይሆናል ነው ያሉት፡፡
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ መኪና ከድምጽ እና ከአየር ብክለት አንጻር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአቤል ነዋይ