15 ሺህ 492 ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር አስመርቀናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምግብ ዋስትናና ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም 15 ሺህ 492 ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር አስመርቀናል አሉ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት፥ አዲስ አበባ ለችግር የተጋለጡ ነዋሪዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች።
ይህ ተግባር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ከተደረጉት አምስቱ የ“ዜሮ ግቦች” መካከል አንዱና ዋነኛው የሆነው ተረጂነትንና ልመናን ዜሮ የማድረግ ታላቅ ራዕይ በከተማችን ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ነው ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በሴፍትኔት ፕሮግራም ውስጥ ተይዘው ሲረዱ የነበሩ ከ695 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ራሳቸውን እንዲችሉና ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ ተደርጓል ነው ያሉት።
በከተማችን የሥራ ልምምድ ከተጀመረበት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ዛሬ የተመረቁትን 8 ሺህ 852 ወጣቶች ጨምሮ 49 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ከተረጂነትና ስራ አጥነት ወጥተው በተፈጠረላቸው ትስስር የሥራ ላይ ልምምድ አጠናቀው ወደ ስራ ባለቤትነትና አምራችነት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከተማችን ያገኙትን ዕድል አሟጥጠው በመጠቀም ሕይወታቸውን በዘላቂነት የሚለውጡና ለሌላውም አርአያ የሚሆኑ ትጉህ ወጣቶች ያስፈልጓታል ብለዋል።
በቀጣይም ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩና ባካበቱት ልምድ የድርጅት ባለቤቶች ጭምር እንደሚሆኑ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡