የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ ሃሳቦቻቸውን ለሕዝብ የሚያቀርቡበትን እድል ለማስፋት…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያዘጋጀው የመጀመሪያው የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በዚህ ወቅት÷ ቦርዱ ባለፉት ጥቂት ወራት የክርክር መድረኩን ለማዘጋጀት ሲሰራ የቆየ ሲሆን÷ይህም በኢትዮጵያ የምርጫ ሒደት ውስጥ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ብለዋል።
ይህ ተነሳሽነት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን አማራጭ የፖሊሲ ሃሳቦች ለሕዝብ የሚያቀርቡበት ዕድል እንደሚፈጥር ነው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም የፓርቲዎቹን አቋም ለማሳወቅ እንደሚረዳና መራጩ ሕዝብ ያደገ ግንዛቤ እንዲኖረው አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል።
ቦርዱ በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመደገፍ የተለያዩ ስልጠናዎችን ጨምሮ ፓርቲዎች የሙከራ ክርክሮችን እንዲያካሄዱ የሚያስችል ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡
መድረኩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ማሕበረሰብ ተወካዮችን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በማገናኘት ለዴሞክራሲያዊ ምህዳር መስፋት አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አብራርተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክር መድረክ ምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ምርጫው ይበልጥ አካታች እና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ እያደረገ ያለው ጥረት አካል ነው ማለታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።