በኮሪደር ልማት ይበልጥ የዘመነችው ቢሾፍቱ …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቢሾፍቱ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን ይበልጥ ውብ፣ ዘመናዊ እና ለኑሮ ምቹ እያደረገ ነው፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ እንደሚሉት÷የኮሪደር ልማቱ የቢሾፍቱን የክትመት ደረጃ በማሳደግ ውብ፣ ጽዱ እና የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን እያደረገ ነው፡፡
ቢሾፍቱ ሰባት የተፈጥሮ ሐይቆች እንዳሏት ጠቅሰው ÷ የከተማዋን የኮንፈረንስ እና የቱሪስት ማዕከልነት ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ ከተማዋን ዘመናዊ ፣ ውብ፣ ምቹ እና ጽዱ እያደረጋት እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡
104 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ለማከናወን ታቅዶ እየተሰራ ነው ያሉት ከንቲባው÷ እስካሁን 87 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ሥራ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
የቢሾፍቱ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ ከተፈጥሮ ጋር በልዩ ሁኔታ የተሳሰረ ነው፤ በተለይም የኮሪደር ልማቱን ከተፈጥሮ ሐይቆች ጋር በማሰናሰል እየተሰራ ያለው ሥራ ከተማዋን ልዩ ውበት አጎናጽፏታል ብለዋል፡፡
ቢሾፍቱን በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ እንድትሆን በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የከተማዋን የኮንፈረንስ ማዕከልነት ይበልጥ ለማጠናከርም ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ ፓርኮችና ሌሎች የመዝናኛ ሥፍራዎች እየተገነቡ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡
የከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማጠናከርና በኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት የፈጠረው ከፍተኛ እንቅስቃሴ ለነዋሪዎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገት በማሳላጥ የነዋሪዎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራም አመልክተዋል።