Fana: At a Speed of Life!

 የኢትዮጵያ የመስኖ ሽፋን ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር አድጓል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የመስኖ ሽፋን ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር አድጓል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ የተገነባው ተንዳሆ የመስኖ ልማት ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ተመርቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በሕዝቡ ዘንድ የቅሬታ ምንጭ ሆነው የሰነበቱ  የመገጭ፣ አርጆ፣ ከሰም፣ ቄጦ፣ ታችኛው ርብ፣ ጊዳቦ እና ጎዴ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለልማት እንዲውሉ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

በመስኖ ዘርፍ ለውጥ ለማምጣት በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እና ቁርጠኛ አመራር እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በአብነትም የተንዳሆ መስኖ ልማት ፕሮጀክት የጥረቱ እና የቁርጠኛ አመራሩ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የዛሬ 15 ዓመት ቢገነባም መሠረታዊ የማጠናቀቂያ ሥራ እንዳልተሰራለት እና ጥገና እንዳልተደረገለት አስታውሰዋል።

በዚህም ምክንያት ያለ ጥቅም ከመቆየቱ በተጨማሪ ውሃን በከፍተኛ ሁኔታ እያከማቸ ለአካባቢው ማህበረሰብ  የጎርፍ ሥጋት ሲፈጥር ቆይቷል ነው ያሉት፡፡

ከለውጡ በኋላ ዘርፉን ለማሳደግ በተሰራው ብርቱ ሥራ ፕሮጄክቱን መጠናቀቁን ጠቅሰው፤ በዚህም የኢትዮጵያ የመስኖ ሽፋን ማደጉን ገልጸዋል።

ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያ የመስኖ ሽፋን ወደ 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር ማደግ መቻሉንም ተናግረዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.